ቻይና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ስለፍቅር ትምህርት እንዲሰጥ ወሰነች
ሀገሪቱ ውሳኔው ላይ የደረሰችው ለፍቅር ግንኙነት እና ለትዳር ያለውን አሉታዊ እሳቤ ለመቀየር ነው ተብሏል
በቻይና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች 57 በመቶዎቹ የፍቅር ግንኙነት መመስረት አይፈልጉም
የቻይና በዩኒቨርስቲ እና ኮሌጆች ውስጥ የፍቅር ትምህርት እንዲሰጥ ወሰኔ አሳለፈች፡፡
ዜጎች በትዳር ፣ በፍቅር ግንኙነት እና ቤተሰብ ላይ አዎንታዊ አመለካከቶችን እንዲያዳብሩ ነው ቤጂንግ ውሳኔው ላይ መድረሷ የተሰማው፡፡
ቻይና በ2023 ለሁለተኛ ተከታታይ አመት የህዝብ ቁጥር መቀነስ ካስመዘገበች በኋላ ልጅ መውለድን ለወጣት ጥንዶች ይበልጥ ማራኪ ለማድረግ የተለያዩ የማበረታቻ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች።
ሀገሪቱ ምንም እንኳን በ1.4 ቢሊየን ህዝብ በአለም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም የውልደት ምጣኔዋ ሲቀንስ በአንጻሩ በእርጅና ላይ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ይገኛል፡፡
በዚህ የተነሳ የስነህዝብ ፖሊሲ ቀውስ ሊያጋጥማት እንደሚችል በስጋት ላይ የምትገኘው ቤጂንግ ቀውሱ በኢኮኖሚው እና በአጠቃላይ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ተንብያለች፡፡
የሀገሪቱን የውልደት ምጣኔ በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የሚጠበቁት የኮሌጅ ተማሪዎች በትዳር እና በፍቅር ላይ ያላቸው ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡
ይህን ለመቀየር ቻይና ከአንድ ልጅ ፖሊሲ ወጥታ ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎች የትዳር እና የፍቅር ትምህርቶችን በመስጠት ወጣቶች በመዋለድ እና ቤተሰብ በመመስረት ዙርያ ያላቸውን ዝቅተኛ ተነሳሽነት ለመቀየር ወጥናለች፡፡
ምንም እንኳን ውሳኔው አወንታዊ ትዳር እና ልጅ የመውለድ ባህልን ለማዳበር እቅድ ቢይዝም የስነ-ህዝብ ተመራማሪዎች የፍቅር ትምህርት መሰጠቱ የወጣት ቻይናውያን አመለካከት የመቀየር ዕድሉ አነስተኛ ነው ብለዋል ።
በቻይና ፖፑሌሽን ኒውስ ከተጠየቁት የኮሌጅ ተማሪዎች መካከል 57 በመቶ የሚሆኑት የፍቅር ግንኙነት መመስረት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ያደረጉት ለፍቅር ግንኙነት እና ለትምህርት የሚሰጡትን ጊዜ እንዴት ማመጣጠን እንደሚችሉ አለማወቃቸው እንዲሁም ከፍቅር እና ቤተሰብ መመስረት በፊት በኢኮኖሚ ራስን ማሻሻል ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ነውተብሏል፡፡
ሳይንሳዊ የጋብቻ እና የፍቅር ትምህርት ባለመኖሩ የኮሌጅ ተማሪዎች ስለ ስሜታዊ ግንኙነቶች ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የላቸውም፡፡
የፍቅር ትምህርቶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ለታዳጊ የኮሌጅ ተማሪዎች ስለ ህዝብ ብዛት እና ሀገራዊ ሁኔታ፣ ስለ አዲስ ጋብቻ እና ልጅ መውለድ ጽንሰ ሀሳቦች በማስተማር ላይ ሊያተኩሩ ይችላሉ፡፡
ኮርሶቹ ትዳርን በትክክል የመረዳት እና የፍቅር ግንኙነቶችን የመምራት ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ሊረዳቸው እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡