የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ወታደራዊ ህግ ካወጁ በኋላ ከስልጣን ተነስተው በህግ እንዲጠየቁ ዜጎች እየጠየቁ ነው
ፕሬዝዳንቱ በትላንትናው ዕለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሰሜን ኮርያ ጋር አደገኛ ሴራ እየወጠኑ ነው በሚል ወታደራዊ እዝ እንድትመራ አዋጅ አውጀው ነበር
ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚያግደው አዋጅ በፓርላማ አባላት እና በዜጎች ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው በሰአታት ውስጥ እንዲነሳ ተደርጓል
የደቡብ ኮርያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዩል ከስልጣናቸው እንዲነሱ እና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚጠይቁ ድምጾች ተበራክተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በትላንትናው እለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ጋር ሀገሪቱን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ግንኙነት ጀምረዋል በሚል ወታደራዊ አዋጅ አውጀው ነበር፡፡
ማክሰኞ መገባደጃ ላይ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ምንም እንኳን የተለየ ስጋት ባይጠቅሱም “ሀገሪቱን ከኒውክሌር ታጣቂዋ ሰሜን ኮሪያ ፣ ከፀረ ደቡብ ኮርያ መንግስት ሃይሎች ለመከላከል እና ነፃ ህገመንግስታዊ ስርአቷን ለመጠበቅ የአስቸኳይ ወታደራዊ አዋጅ (ማርሻል ህግ) መታወጁን” ገልጸዋል፡፡
ቆየት ብሎም ገዥው ፓርቲ “ፒፕል ፓወር ፓርቲ” የመከላከያ ሚኒስትሩ ኪም ዮንግ-ህዩን መባረራቸውን እና አጠቃላይ ካቢኔው መበተኑን ይፋ አድርጓል፡፡
አዋጁን ተከትሎ የሀገሪቱ ጦር ልዩ ሀይል አባላት የፓርላማውን ህንጻ ለመቆጣጠር ሲሞክሩ እና የአዋጁ ተቃዋሚዎች በፓርላማው አቅራቢያ ከፖሊሶች ጋር ሲጋጩ ታይተዋል፡፡
የፓርላማ አባላት እና ዜጎች አዋጁን በመቃወም ባደረሱት ከፍተኛ ተጽዕኖ ከሰአታት በኋላ አዋጁ ቢሻርም በፕሬዝዳንቱ ላይ እየደረሱ ያሉ ተቃውሞ እና ተጽዕኖዎች በርትተዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ መግለጫውን በተናገሩ በሰዓታት ውስጥ የደቡብ ኮሪያ ፓርላማ ከ300 አባላቶቹ 190 ያህሉ በተገኙበት አዋጁ እንዲነሳ የቀረበው ጥያቄ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል። ከዚያም ፕሬዚዳንቱ አዋጁን ሽረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከሀገር ውስጥ እስከ አለም አቀፍ ደረጃ በተጽዕኖ ውስጥ የሚገኙት ዮን ሱክ ዩል ከስልጣናቸው እንዲነሱ እና በህግ ተጠያቂ እንዲደረጉ ጥሪ እየቀረበባቸው ነው፡፡
ስድስት የደቡብ ኮሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንቱ ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ የሚጠይቅ ሰነድ በዛሬው እለት ለፓርላማው እንደሚያስገቡ የተነገረ ሲሆን በጥያቄው ዙርያ አርብ ወይም ቅዳሜ ምክር ቤቱ ድምጽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
በሀገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው “ዲሞክራቲክ ፓርቲ” ከ2022 ጀምሮ በስልጣን ላይ የሚገኘው የዮን ሱክ ዩል አስተዳደር ስልጣን እንዲለቅ ወይም እንዲከሰስ ጠይቋል።
“ፓርቲው ፕሬዝዳንት ሀገሪቱን በመደበኛነት መምራት እንደማይችሉ ለመላው ህዝብ በግልፅ አሳይተዋል” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡
አሜሪካ በእስያ አህጉር ዋነኛ ወታደራዊ አጋሯ የሆነችው ሴዑል ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታ እንዳሳሰባት ተናግራለች። የፕሬዝዳንቱ አስተዳደር እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተፈጠሩ ልዩነቶችን በውይይት እንዲፈቱም ጠይቃለች፡፡
ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ምክንያታዊ አለመሆኑን ላይ በፊት ለፊት እና በተዘዋዋሪ ትችታቸውን እየሰነዘሩ እንደሚገኙ የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡