ሩሲያ እና አሜሪካ የሶሪያውን ጦርነት በማባባስ በተመድ እርስበእርስ ተካሰሱ
ሀያት ታህሪር አል-ሻም በጀመረው ጥቃት የሶሪያ አማጺያን አሌፖ የተባለችውን ከተማ ባለፈው ሳምንት ተቆጣጥረዋል
የሩሲያ እና የአሜሪካ ግንኙነት፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተችበት ከ2022 ወዲህ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቷል
ሩሲያ እና አሜሪካ በትናንትናው እለት በተመድ በተካሄደው የጸጥታ ምክርቤት ስብሰባ ላይ በቅርቡ በሶሪያ የተቀሰቀሰው ጦርነት እንዲባባስ ሽብርተኝነትን በመርዳት እርስ በእርሳቸው ተካሰዋል።
ሀያት ታህሪር አል-ሻም በጀመረው ጥቃት የሶሪያ አማጺያን አሌፖ የተባለችውን ከተማ ባለፈው ሳምንት ተቆጣጥረዋል። ቀደም ሲል ኑስራ ግንባር በመባል የሚታወቀው ሀያት ታህሪር አል-ሻም በ2016 ከመገንጠሉ በፊት በሶሪያ ይፋዊ የአልቃ ኢዳ ክንፍ ነበር። በተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ማዕቀብ ተጥሎበታል።
በተመድ የአሜሪካ ምክትል አምባሳድር ሮበርት ውድ በሶሪያ ያለው ግጭት እንዲቆም እና ንጹሃን ከጥቃት እንዲጠበቁ ጥሪ አድርገዋል። የአማጺያኑ እንቅስቃሴ በሀያት ታህሪር አልሻም መመራቱም እንዳሰጋቸው አምባሳደሩ ገልጸዋል።
"ሀያት ታህሪር አልሻም በአሜሪካ እና በተመድ ሽብርተኛ ተብሎ መፈረጁ ብቻ በአሳድ አገዛዝ እና በሩሲያ የሚፈጸሙ ግፎችን ምክንያታዊ አያደርጋቸውም" ያሉት ውድ የሶሪያውን ፕሬዝደንት በቭር አላሳድን እና ሩሲያን በትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ላይ ጥቃት በማድረስ ከሰዋል።
የሩሲያው የተመድ አምባሳደር ቫሳሊ ነበንዚያ ለውድ በሰጡት ምላሽ" በሰላማዊ የሶሪያ ከተሞች ላይ የደረሰውን የሽብር ጥቃት ለማውገዝ ወኔ የለህም" ብለዋል።
"ዋሽንግተን አለምአቀፍ ሽብርተኝነት ትዋጋለች የሚል እምነት የለም" ሲሉ ንበንዚያ ተናግረዋል።"ግልጹን ለመናገር አሁን ላይ ከእናንተ በተቃራኒ በመቆማችን ደስተኞች ነን።"
አምባሳደር ወድ በበኩላቸው ነበንዚያ "በዚህ ጉዳይ እኛን ሊያስተምር አይችለም"፤ ምክንያቱም ሞስኮ "በመላው አለም ሽብርተኞችን የሚረዱ አገዛዞችን ትረዳለች" ሲሉ መልሰዋል።
አምባሳደሩ አሜሪካ ለበርካታ አስርት አመታት በመላው አለም ሽብርተኝነትን መዋጋቷን እና ይህንኑ ተግባሯን እንደምትገፋበት ተናግረዋል።
የሩሲያ እና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተችበት ከየካቲት 2022 በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቷል።