የመካከለኛው እስያ ሀገራት ለቻይና በአማራጭ የንግድ ኮሪደር ታጭተዋል
የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በመካከለኛው እስያ መሠረተ ልማት ከመገንባት እስከ ንግድ እድገት የሚሸፍን የልማት እቅድ አውጥተዋል።
እቅዱ በተለምዶ በሩስያ ተጽዕኖ ስር በሆነው ክልል ውስጥ አዲስ የመሪነትን ሚና ለመያዝ ነው ተብሏል።
ዢ በቻይና-ማዕከላዊ እስያ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ቻይና ከካዛኪስታን፣ ኪርገስታን፣ ታጂኪስታን፣ ቱርክሜኒስታን እና ኡዝቤኪስታን ጋር የልማት ስልቶችን ለማስተባበር እና ዘመናዊ አሰራርን ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።
"ይህ ጉባኤ በስድስቱ ሀገራት ልማት ላይ አዲስ መነሳሳትን የጨመረ ነው። ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት ጠንካራ አዎንታዊ ኃይል ያመጣ ነው” ሲሉ ዢ ተናግረዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት መወጠርና የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን መውጣት ቻይና በሀብት የበለጸገው ክልል ውስጥ ለፖለቲካ ተጽእኖ እና ለኃይል እሽቅድምድም ከፊት ተሰላፊ ሆናለች።
አምስቱ የቀድሞ የሶቪየት ህብረት ሀገራት ለቻይና ነዳጅ፣ ምግብና ሌሎች ሸቀጦችን ለማጓጓዝ አማራጭ ኮሪደር ናቸው።