ቻይና ስድስት የአየር ክልሎችን አደገኛ ብላ መሰየሟንም አስታውቃለች
በታይዋን አቅራቢያ የሚበሩ አውሮፕላኖች በረራ እንዲያቆሙ የቻይና መንግስት ማሳሰቢያ ሰጠ።
ቤጅንግ፤ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባዔ የታይዋን ጉብኝትን ተከትሎ ወታደራዊ ልምምድ ስለሚኖር አየር መንገዶች በረራ ማቆም እንዳለባቸቀው አሳስባለች። ቻይና ስድስት የአየር ክልሎችን አደገኛ ብላ መሰየሟንም አስታውቃለች፡፡
በእስያ አህጉር የሚሰሩ አየር መንገዶች ከፈረንጆቹ ነሐሴ አራት እስከ ነሐሴ 7 ቀን አደገኛ ተብለው በተለዩ የአየር ክልሎች መብረር እንደሌለባቸውም ቤጅንግ አሳውቃለች።
ቻይና አደገኛ የአየር ክልል ብላ የለየቻቸው ስድስት የአየር ክልሎች ወታደራዊ ልምምድ የሚደረግባቸው መሆናቸውንም ገልጻለች።
የቻይና ጦር ወታደራዊ ልምምድ የሚያደርግባቸውን አየር ክልሎች በሀገሪቱ ዜና አገልግሎት ሽንዋ በካርታ መልክ ይፋ ተደርገዋል።
በቀጠናው ያሉ አየር መንገዶች መያዝ ካለባቸው የነዳጅ መጠን በላይ ለ30 ደቀቃ የሚሆን ተጨማሪ ነዳጅ እንዲይዙ እንደተነገራቸው ብሉምበርግ ዘግቧል።
አየር መንገዶቹ ተጨማሪ ነዳጅ እንዲይዙ የተነገራቸው አየር ላይ በሚነገራቸው መመሪያ መሰረት የመብረሪያ ክልል እንዲቀይሩና እንዲያስተካክሉ ለማድረግ ነው ተብሏል።
ወደ ቻይና ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የሚደወሉ ጥሪዎችና መልዕክቶች እየተመለሱ እንዳልሆነም ብሉምበርግ ዘግቧል።
በ25 ዓመት ውስጥ አንድ ከፍተኛ አሜሪካ ባለስልጣን ወደ ታይዋን ሲያቀኑ ፔሎሲ የመጀመሪያዋ መሆናቸው ተገልጿል። በአፈጉባዔዋ ጉብኝት የተከፋችው ቻይና ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ምላሽ ልትሰጥ እንደምትችል ማስጠንቀቋን ቀጥላለች።
በቤጅንግ እና በዋሸንግተን መካከል ብዙ ልዩነቶች ቢኖሩም እጅግ ወቅታዊውና ስሜት ኮርኳሪው የታይዋን ጉዳይ ነው።