ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት 300 ሺህ ቶን ስንዴ እና በቆሎ እንደተበላሸባት ገለጸች
የስንዴ ምርቱ በተቀመጠበት መጋዝን ውስጥ የተበላሸው በሩሲያ ጥቃት ምክንያት መሆኑን ዩክሬን ገልጻለች
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 107 ቀናት ሆኖታል
ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት 300 ሺህ ቶን ስንዴ እና በቆሎ እንደተበላሸባት ገልጸች፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች 107 ቀናት ተቆጥረዋል።
ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ብቻ የሩሲ ጦር ባደረሰው ጉዳት ምክንያት 300 ሺህ ቶን ስንዴ እና በቆሎ ከጥቅም ውጪ መሆኑን የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ታራስ ቬሶቲክዬ ለሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን እንዳሉት የዩክሬን በጥቁር ባህር ባለ የጥራጥሬ ማከማቻ ውስጥ ያጠራቀመችው 300 ሺህ ቶን ስንዴ እና በቆሎ በሩሲያ ጦር ወድሟል ብለዋል፡፡
ሩሲያ በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም፡፡
የሁለቱ ሀገራት ጦርነት በተቀረው ዓለም ላይ ጉዳት በማድረስ ላይ ሲሆን በተለይም የምግብ እና ነዳጅ ዋጋ እንዲያሻቅብ እያደረገ ይገኛል፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን መኖሪያቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ 20 በመቶ የዩክሬን ክፍልም በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር መውደቁን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት መሰረት መኖሪያ ቤታቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት ሀገራት ከተሰደዱ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን መካከል 2 ነጥብ 5 ያህሉ ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል፡፡በጦርነቱ እስካሁን ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ5 ሺህ በላይ ንጹሃን ደግሞ እንደቆሰሉ የዚሁ ተቋም ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በዚህ ጦርነት ምክንያት የምግብ ዋጋ ካሻቀበባቸው ሀገራት መካከል አፍሪካ አንዷ ስትሆን ከሰሞኑ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ወደ ሞስኮ አቅንተው ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር መምከራቸው ይታወሳል፡፤
ዩክሬን በኦዴሳ ወደብ ላይ ያጠመደቻቸውን ፈንጂዎች ካላነሳች ከሩሲያ እና ዩክሬን በሚገባ የስንዴ ምርት ላይ ጥገኛ የሆነችው አፍሪካ ወደ ከፋ ረሃብ ልታመራ ትችላለች ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ክጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት መግለጫ አሳስበዋል፡፡