ፔሎሲ ታይዋንን ከጎበኙ ጦሯ “ዝም ብሎ እንደማይቀመጥ” ቻይና አስጠንቅቃለች
ቻይና የአሜሪካ አፈጉባኤ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ያለው ሁኔታ " ወደ አስከፊ የፖለቲካ ተጽእኖ ያመራል" ሰትል ተደምጣለች
የአሜሪካ አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ "የአሜሪካ መንግስት ቁጥር 3 ባለስልጣን" መሆናቸው የታወቃል
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ጦሯ “ዝም ብሎ እንደማይቀመጥ” ቻይና አስጠንቅቃለች፡፡
ቻይና ይህን የማስጠንቀቅያ መልዕክት ያስተላለፈቸው በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን በኩል ነው፡፡
ቃል አቀባይ ዣኦ ሊጂያን ፔሎሲ "የአሜሪካ መንግስት ቁጥር 3 ባለስልጣን" እንደመሆናቸው ቻይና የራሴ ገዛት ናት ብላ የምትቆጥራትን ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ሁኔታው "ወደ አስከፊ የፖለቲካ ተጽእኖ ያመራል" ብለዋል።
የአሜሪካ አፈጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ የእስያ ጉዟቸውን ቅዳሜ እለት መጀመራቸው ሮይተርስ መዘገቡ አይዘነጋም፡፡የአፈጉባኤዋ የሩቅ ምስራቅ ሀገራት የመጎብኘት ጉዞ ሲንጋፖርን፣ ማሌዥያን ፣ ደቡብ ኮሪያንና ጃፓን እንደሚያካትትም ነበር አፈጉባዔዋ የገለጹት፡፡
የጉዟቸው ዓላማ በአሜሪካ እና በሀገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የገለጹት ናንሲ ፔሎሲ፤ በእስያ ጉብኝታቸው ታይዋንን እንደሚጎበኙ ቀደም ብለው ገልጸው የነበረ ቢሆንም በአሁኑ የጉዞ ዝርዝር ግን ታይዋን አልጠቀሱም።
አፈጉባዔዋ በጉዞ ታይዋንን ያልጠቀሱት ከቻይና በተሰነዘረ የማስፈራሪያ ዛቻ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። ናንሲ ፔሎሲ ወደ ታይዋን ከሄዱ ቤጅንግ እርምጃ እንደምትወስድ ማስጠንቀቋን ተከትሎ ውጥረቱ አይሏል።
ቻይና በታይዋን ጉዳይ እንደማትደራደር በተደጋጋሚ ስትገልጽ አሜሪካ ደግሞ ታይዋንን የሚነካ ብሔራዊ ጥቅሜን የነካ ነው እያለች ነው።
ከሰሞኑ የስልክ ውይይት ያደረጉት የቻይና እና የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በጭቅጭቅ የተሞላ ውይይት አድርገዋል።የሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የንግግር ርዕስ ታይዋን የነበረች ቢሆንም በተለመደ ያለመስማማት መንፈስ ንግግራቸውን ጨርሰዋል ተብሏል።