ቻይና፤ የአሜሪካ ም/ ቤት አፈጉባዔ ታይዋንን ከጎበኙ እርምጃ እወስዳለሁ ስትል አስጠነቀቀች
አሜሪካ ለታይዋን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠቷ ከቻይና ጋር እያጋጫት ነው ተብሏል
የአሜሪካ እና የቻይና ፕሬዝዳንቶች በታይዋን ጉዳይ ተወያይተው ነበር
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባዔ ታይዋንን የሚጎበኙ ከሆነ ቻይና ጠንካራ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች፡፡
ከሰሞኑ አፈጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ ታይዋንን ይጎበኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን ቻይና ግን ይህንን ተቃውማለች፡፡ የፔሎሲ ጉብኝት እውን የሚሆን ከሆነ የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ይጎዳል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛኦ ሊጃን ፤ አሜሪካ ከታይዋን ጋር የምታደርገውን መቀራረብ ቻይና እንደምትቃወም ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት የአሜሪካ አፈጉባዔ ወደ ታይዋን ያደርጉታል የተባለውን ጉብኝት መሰረዝ አለባቸው ብለዋል፡፡
አሜሪካ ከታይዋን ጋር ያላትን መቀራረብ የማታቆም ከሆነ ቻይና ሉዓላዊነቷንና ግዛታዊ አንድነቷን ለማስከበር ስትል ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ ገልጻለች፡፡
ቤጅንግ የምትወስደው ማንኛውም እርምጃ መነሻው የአሜሪካ ህገ ወጥ አካሄድ እንደሆነ ሊታወቅ እንደሚገባም የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል፡፡
ቻይና ታይዋን ራስ ገዝ አስተዳደር ብትሆን የራሷ አካል እንደሆነች ብትገልጽም ጉዳዩ ዋሸንግተንና ቤጅንግን እያወዛገበ ይገኛል፡፡ አሜሪካም ለታይዋን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠቷ የሀገራቱን ፍጥጫ አንሮታል እየተባለ ነው፡፡
ምንም እንኳን ቻይና የፔሎሲን ጉብኝት ብትቃወምም ጉብኝታቸውን በተመለከተ ግን ከአፈጉባዔዋ ቢሮ የተሰጠ መግለጫ የለም ተብሏል፡፡ ፔሎሲ ለመጨረሻ ጊዜ ታይዋንን የጎበኙት በአውሮፓውያኑ 1997 ነበር፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንትና የቻይናው አቻቸው አድርገውት በነበረው የበይነ መረብ ውይይት፤ ዋሸንግተን በቤጅንግ የውስጥ ጉዳይ እንደማትገባ መግባባት ላይ ደርሰው እንደነበር ሲጂቲኤን መዘገቡ ይታወሳል፡፡