ዩክሬን፤ ሩሲያ በደቡብ ዩክሬን በሚገኘው የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሳለች ስትል ከሰሰች
የዩክሬን ኒውክሌር ኤጀንሲ፤ በጥቃቱ በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብሏል
ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ፤“ሩሲያ መላውን ዓለም አደጋ ላይ እየጣለች ነው፤ ይህ ነገር ጊዜው ሳይረፍድ ማቆም አለብን"ብለዋል
ዩክሬን፤ሩሲያ በደቡብ ዩክሬን ማይኮላይቭ ግዛት በሚገኘውን የፒቭደንኑክራይንስክ የኒውክሌር ጣቢያ ላይ ጥቃት አድርሳለች ስትል ከሰሰች፡፡
ከጣቢያው 300 ሜትር ርቀት ላይ የደረሰው ጥቃት በአቅራቢያው በሚገኝ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ እና ማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም ህንጻዎች ላይ ጉዳት አድርሷልም ነው የተባለው፡፡
ነገር ግን ጥቃቱ ከባድ የሚባል ባለመሆኑ የኃይል ማመንጫዎቹ ጉዳት ብዙም እንዳልተጎዱ እና በመደበኛነት እየሰሩ መሆናቸውን የዩክሬን የኒውክሌር ኤጀንሲ /ኢነርጎአቶም/ አስታውቋል።
ኤጀንሲው፤ "በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የፒኤንፒፒ (ፒቭደንኑክራይንስክ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ) ሶስቱም የኃይል ዪኒቶች በመደበኛነት እየሰሩ ናቸው፤ እንደ እድል ሆኖ በጣቢያው ሰራተኞች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም" ብሏል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በቴሌግራም ቻናል ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ወራሪዎች እንደገና መተኮስ ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ምን እንደሆነ ረስተዋል፤ ሩሲያ መላውን ዓለም አደጋ ላይ እየጣለች ነው፤ ይህ ነገር ጊዜው ሳይረፍድ ማቆም አለብን " ሲሉ መናገራቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
የክሬምሊን ሰዎች ለዩክሬን ክስ እስካሁን የሰጡት ምላሽ የለም፡፡
የማይኮላይቭ ግዛት በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በሩሲያ ኃይሎች የማያቋርጥ የሮኬት ጥቃት የደረሰበት አከባቢ ነው።
በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የሚገኘው ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያም ቢሆን ከማይኮላይቭ ግዛት 250 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እብደሚገኝ የሚተወቅ ነው፡፡
እናም እናም በጦርነት ውስጥ የሚገኙትና እርስ በርስ የሚካሰሲት ሩሲያና ዩክሬን፤ በኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት ከሀገራቱ በዘለለ ለተቀረው ዓለም ያልተፈለገ መዘዝ ይዞ እንዳይመጣ ተስግቷል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንትቮሎዲሚር ዘለንስኪ ፤ ዓለም በሩስያ ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዛፖሪዝሂያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመከላከል ምንም ዓይነት እርምጃ ካልወሰደ፤ “በሽብርተኞች ይሸነፋል” ሲሉ በቅርቡ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ዓለም አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰደ "በሽብርተኞች ይሸነፋል እንዲሁም እና ለኒውክሌር ጥቃት እጁን ይሰጣል" ሲሉም ነበር የተደመጡት ዘሌንስኪ።
የዩክሬን መሪ ይህን ይበሉ እንጂ የክሬምሊን ባለስልጣናት ግን በኒውክሌር ጣቢያዎች አከባቢ ያለው ውጥረት እንዲቀንስ ከተፈለገ “ዓለም በዩክሬን ላይ ጫና ማድረግ አለበት” በማለት ላይ ናቸው፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በቅረቡ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ "የዩክሬን ታጣቂ ሃይሎች የኒውክሌር ጣቢያን ማውደም ከዩክሬን ባለፈ ለአውሮፓ ምድር እጅግ አደገኛ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው”ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
የዩክሬን አጋሮች "እንዲህ ዓይነቱ የዩክሬን እርምጃ እንዳይቀጥል ተጽእኖ ያድርጉ" ሲሉም ጠይቀው ነበር።