የዩክሬን ፕሬዝዳንት ፤ ፑቲን “ዜጎችን ወደ ሞት እየላኩ ነው” አሉ
ፕሬዝዳንቱ የሩሲያ ኃይሎች እጃቸውን ለዩክሬን ከሰጡ በሰለጠነ መንገድ ይሰተናገዳሉ ብለዋል
ዘለንስኪ የሩሲያ ኃይሎችን “ የጦር ወንጀለኛ ሆኖ ከመሞት የውትድርና ደብዳቤን አለመቀበል ይሻላል” ሲሉ መክረዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ፤ ቭላድሚር ፑቲን እያወቁ “ዜጎችን ወደ ሞት እየላኩ ነው” አሉ፡፡
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ትናንት ምሽት በሩሰያኛ ባደረጉት ንግግር የፑቲን የክተት ጥሪ ሩሲያውያንን ሆን ተብሎ ወደ ጦርነት የመማገድ ጥሪ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ፑቲን እያወቁ “ዜጎችን ወደ ሞት እየላኩ ነው” ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ፤ የሞስኮ ኃይሎች እጃቸው እንዲሰጡ መጠየቃቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
“እጃችሁ ከሰጠቻሁ በሰለጠነ መንገድ ትስተናገዳላችሁ… ስለተማረካችሁበት አጋጣሚ ማንም ሰው አያውቅም” ሲሉም ነው የሩሲያ ጦር አባላት ለዩክሬን ጦር እጃቸው እንዲሰጡ መልዕከት ያስተላለፉት ዘለንስኪ፡፡
አክለውም “በውጭ ሀገር የጦር ወንጀለኛ ሆኖ ከመሞት የውትድርና ደብዳቤን አለመቀበል ይሻላል” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
የዩክሬን ኃይሎች በሩሲያ ጦር ላይ የጀመሩት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ተከትሎ የተፈጠው የኃይል ሚዛን ፤ በክሬምሊን ሰዎች በኩል ከፍተኛ ድንጋጤት ሳይፈጥር እንዳልቀረ በመነገር ላይ ነው፡፡
ፑቲን ለተፈጠረው ውድቀት ተጠያቂ ነው ያሏቸውንና የጦር መሳሪያ ሎጂክስቲክስን ይመሩ የነበሩትን የመከላከያ ምክትል ኃላፊን ማባረራቸው ተሰምቷል፡፡
ያም ሆኖ የክሬምሊን ባለስልጣናት አሁንም ቢሆን በዩክሬን ለማሳካት ያቀድነውን ዓላማ እውን ለማድረግ ሚያስቆመን ማንምኛም ኃይል የለም እያሉ ነው፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ “የኒውክሊየር መሳሪያ”ን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በቅርቡ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት ድርጊቶች የተፈጸሙበት ደም አፋሳሽ ጦርነት እንደሆነ የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ ከቀናት በፊት ተመድ የጸጥታው ም/ቤት ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በዩክሬን ጦርነት ውስጥ የተፈጸመው “ጭካኔዎች” ምርመራ እንዲካሄድ አስስበዋል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብት አካል ሪፖርቶች “ በዩክሬን ጦርነት ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት፣ ማሰቃየትና ሌሎች በሰላማዊ ሰዎች እና የጦር እስረኞች ላይ ኢሰብዓዊ ድርጊቶች መፈጸማቸው ያሳያሉ” ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ ተፈጽሟል የተባሉት ጭካኔዎች ላይ ዝርዝር ምርመራ ሊካሄድ ይገባልም ብለዋል፡፡
ጣቶችን ወደ ሩሲያ ሳይቀስሩ "ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እነዚህ ሁሉ ክሶች በጥልቀት መመርመር አለባቸው" ብለዋል ዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፡፡
ጉቴሬዝ፤ ወንጀለኞች በፍትሃዊ እና ገለልተኛ የፍርድ ሂደቶች ሊጠየቁ ይገባል እንዲሁም ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ፍትህ የማግኘት፣ የማገገሚያና ካሳ የማግኘት መብት አላቸው ሲሉ መናገራቸውም ይታወሳል፡፡