ቻይና ባለፉት ሶስት ዓመታት በደሴቲቱ አቅራቢያ ያላትን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጨምራለች
የቻይናው ጠቅላይ ሚንስትር ሊ ኬኪያንግ ከታይዋን ጋር “ሰላማዊ ውህደት” ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የታይዋንን ነፃነት በመቃወም ቆራጥ እርምጃዎችን እንደሚወስዱም ቃል ገብተዋል።
ታይፔ በበኩሏ ቤጂንግ የታይዋንን ህዝብ ዲሞክራሲ እና ነጻነት ማክበር አለባት ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
ታይዋንን የራሴ ግዛት የምትለው ቻይና፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት በደሴቲቱ አቅራቢያ ያላትን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጨምራለች።
ይህም በታይፔ እና በዋሽንግተን መካከል አለ ላለችው "ትብብር" ምላሽ ለመስጠት ነው ብላለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ሊ በቻይና ፓርላማ ዓመታዊ ስብሰባ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ቤጂንግ “አንድ ቻይና” በሚለው መርህ ላይ እንደምትጸና ገልጸዋል።
መርሁ ታይዋን የቻይና አካል መሆኗን ይገልጻል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው በቀጥታ ወታደራዊ እርምጃን በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።
መንግስት “የታይዋንን ጥያቄ ለመፍታት” የፓርቲያችንን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ “የታይዋንን ነጻነት በመቃወም ቆራጥ እርምጃዎችን በመውሰድ ዉህደትን መደገፍ አለበት” ሲሉ ወደ ሦስት ሽህ ለሚጠጉ ልዑካን ተናግረዋል።
"ባህር ተሻጋሪ ግንኙነቶችን በሰላማዊ መንገድ ማጎልበት እና የቻይናን ሰላማዊ የውህደት ሂደትን ማሳደግ አለብን" ብለዋል።
ሮይተርስ እንደዘገበው አብዛኛው የታይዋን ህዝብ በቻይና የመግዛት ፍላጎት የለውም።
ቻይናም ደሴቲቱን በእሷ ቁጥጥር ስር ለማድረግ የኃይል እርምጃ መጠቀምን ከአማራጮች ፈጽሞ አልተወችም ተብሏል።
የታይዋን ፕሬዚደንት ሳይ ኢንግ-ወን ከቻይና ጋር ለመነጋገር ደጋግመው ጥሪ ማቅረባቸው የተነገረ ሲሆን፤ ቤጂንግ ደሴቲቷን ተገንጣይ መሆኗን ስላመነች ውድቅ አድርጋለች ተብሏል።
የታይዋን መንግስት የቤጂንግን የይገባኛል ጥያቄ አጥብቆ የሚቃወም ሲሆን፤ እጣ ፈንታዋን የደሴቲቱ 23 ሚሊዮን ህዝብ ብቻ ሊወስን ይችላል ብሏል።
ታይዋን በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ ላይ ፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ምርጫ ታካሂዳለች። በምርጫው ጫና ለማሳደር ሲባል ከቻይና ጋር ያለው ውጥረት እንደሚባባስ ከወዲሁ ይጠበቃል።