የታይዋን መከላከያ ሚኒስትር ቻይናን አስጠነቀቁ
ሚኒስትሩ ቹይ ኩ ቼንግ የታይዋን ጦር በዚህ አመት ከቻይና ሊቃጣ ለሚችል “ድንገተኛ ወረራ” ዝግጁ እንዲሆንም አዘዋል
ቻይና በበኩሏ “ሉአላዊነቴንና የግዛት አንድነቴን ለማረጋገጥ ጠንካራ እርምጃ እወስዳለሁ” ብላለች
ታይዋን ከቻይና ሊቃጣ ለሚችል ጥቃት ጦሯ ዝግጁ እንዲሆን አሳሰበች።
የራስ ገዟ ደሴት መከላከያ ሚኒስትር ቹይ ኩ ቼንግ ናቸው ፥ ታይፒ በዚህ አመት ሊቃጣ ለሚችል “ድንገተኛ ወረራ” ዝግጁ እንድትህን ያሳሰቡት።
ሚኒስትሩ በፓርላማ ከህግ አውጪዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ ቻይና የታይዋንን የባህር እና የአየር ክልል ጥሳ ለመግባት የምታደርገው ጥረት መጠናከሩን አንስተዋል።
የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በየእለቱ የሚያደርጉትን ቅኝት በማሳደግ በዚህ አመት ከታይፒ የባህር ዳርቻ 44 ኪሎአሜትር ላይ ርቆ የሚገኘውን የአየር ክልል ጥሰው ሊገቡ እንደሚችሉም ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።
በታይዋን ሰርጥ ውጥረት እንዲነግስ እያደረግች ነው ያሏትን ቤጂንግም ከድርጊቷ ትታቀብ ዘንድ ማሳሰባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ቻይና በየቀኑ ከ10 በላይ የጦር አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን ወደ ታይዋን አካባቢ ትልካለች ያሉት ሚኒስትሩ፥ አንዳንዶቹ በተለምዶ የተሰመረውን የአየር ክልል እንደሚጥሱ ተናግረዋል።
የቻይና ድሮኖች ወይንም ፊኛዎች የአየር ክልሉን ጥሰው ካለፉ ግን ታይፒ ፈጣን እርምጃ እንደምትወስድም ዝተዋል።
ሚኒስትሩ ታይዋን ከአሜሪካ ጋር እያደረገችው ስላለው የጦር መሳሪያ ግዥ ድርድር ተጠይቀውም ማብራሪያ ከመስጠት መቆጠባቸው ተገልጿል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ለሚኒስትሩ ማብራሪያ በሰጡት ምላሽ ፥ “ቤጂንግ ሉአላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን ለማስጠበቅ ጠንካራ እርምጃ ትወስዳለች” ብለዋል።
የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃል አቀባይ የነበሩት ናንሲ ፔሎሲ ባለፈው አመት በታይዋን ያልተጠበቀ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ በታይዋን ሰርጥ ውጥረት ነግሷል።