ቻይና በወንጀል የተጠረጠሩ ዲፕሎማቶቿን ከብሪታኒያ አስወጣች
በቅርቡ ቦብ ቻን በመባል የሚታወቅ አንድ የሆንግ ኮንግ ተቃዋሚ በቻይና ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ መደብደቡ የሚታወስ ነው
ቻይና ዲፕሎማቶቹን ዞር ማድረጓ ብሪታኒያ ለጉዳዩ የሰጠችውን ክብደት የሚያመላክት ነው ተብሏል
ቻይና በወንጀል የተጠረጠሩ ዲፕሎማቶቿን ከብሪታኒያ አስወጣች።
ቻይና በሰሜን ማንቸስተር ከተማ በሚገኘው የቻይና ቆንስላ ጽህፈት ቤት የተፈጸረውን ብጥብጥና የተፈጸመውን ድብደባ ተከትሎ በወንጀል የተጠረጠሩ ስድስቱን ዲፕሎማቶቿን ከብሪታኒያ አስወጣች፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት 16 ከሆንግ ኮንግ የመጣ አንድ ቦብ ቻን በመባል የሚታወቅ የዴሞክራሲ ደጋፊ ተቃዋሚ በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ እንደተደበደበና ጉዳት እንደደረሰበት የሚታወስ ነው፡፡
ቦብ ቻን ከደበደቡት ወንዶች አንዱ የቆንስላው ኃላፊ ዠንግ ሺዩን እንደነበሩም መገናኛ ብዙሃን በምስል የተደገፉ መረጃዎች ሲያሰራጩ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
የቆንስላ ጄኔራሉ ዠንግ ሺዩን ግን በቦብ ቻን ላይ የፈጸሙት ጥቃትም ሆነ የድብደባ ድረጊት እንደሌለ በመናገር የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎችን ውድቅ አድርገዋል፡፡
በቦብ ቻን ላይ የተፈጸመ የድብደባ ድርጊትን ተከትሎ የሀገሪቱ ፖሊስ ግለሰቡ እንዴት እንደተጎዳ ለመመርመር የዲፕሎማቶቹን ይፋዊ ያለመከሰስ መብታቸውን እንዲነሳ ጠይቆ ነበር፡፡
ይሁን እንጅ ቻይና ቆንስላ ጄኔራል ዠንግ ሺዩንን ጨምሮ ስድስቱን ዲፕሎማቶቿ ወደ ሀገራቸው ማስወጣቷ እየተነገረ ነው፡፡
የቻይና ኤምባሲ በሰጠው መግለጫ ሚስተር ዠንግ ወደ ቻይና መመለሳቸው “የቻይና ቆንስላ ዲፕሎማቶች መደበኛ የሰራ ስምሪት አካል ነው” ብሏል።
ቻይና ዲፕሎማቶቹን ዞር ለማድረግ የወሰደችው እርምጃ በሁለቱም ሀገራት መካከል ሊፈጠር የሚችለውን አለመግባባት ለማቀነስ የተደረገ ሙከራ እንደሆነ ይገመታል፡፡
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክለቨርሊ፡ ቻይና ሚስተር ዠንግን ጨምሮ ሌሎች ዲፕልማቶች ማስወጣቷ ብሪታኒያ ለጉዳዩ የሰጠችውን ክብደት የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡
" በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በሀገር ውስጥ የህግ የበላይነትን ማክበራችን እንቀጥላለን ፤ ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደረጉ እንጠብቃለን " ሲሉም ነው ክለቨርሊ ለሀገሪቱ ፓርላማ ባስተላለፉት የጽሁፍ መግለጫ የተናገሩት፡፡
ኤምባሲው ይህን ይበል እንጅ የቻይና ድርጊት በለንደን እና ቤጂንግ መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያበላሽ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ባለፈው ወር ባደረጉት ንግግር ከቻይና ጋር ያለው “ወርቃማ የግንኙነት ዘመን” ማብቃቱን መናገራቸው አይዘነጋም፡፡