አንጎላ፣ ጅቡቲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ከቻይና በመበደር ቀዳሚዎቹ ናቸው
ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት ያበደረችውን ከወለድ ነጻ ገንዘብ መሰረዟን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ፡፡
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በቅርቡ በተካሄደው የቻይና አፍሪካ ጉባዔ ላይ ፤ሀገራቸው ለአፍሪካ ሀገራት የሰጠችውን ብድር መሰረዟን ይፋ አድርገዋል፡፡ ዋንግ ይ ባሳወቁት መሰረት የ17 ሀገራት ከወለድ ነጻ ብድር ሙሉ ለሙሉ ተሰርዟል፡፡
የቻይና መንግስት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያለውን አጋርነት እንደሚጠናክር የገለጹት ዋንግ ይ፤ የፋይናንስ ድጋፍ እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡
ቻይና ዕዳ የሰረዘችላቸው ሀገራት ይፋ ባይደረግም፣ ቁጥራቸው ግን 17 እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አንጎላ፣ ጅቡቲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ከቻይና በመበደር ቀዳሚዎቹ ናቸው ተብሏል፡፡ ቻይና፤ ለአፍሪካ ሀገራት ከወለድ የሰጠችውን ብድር መሰረዟ ለሀገራቱ አጋርነት ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቤጅንግ ለ 17 የአፍሪካ ሀገራት የምግብ እርዳታ እንደምታደርግ ገልጻለች፡፡
ቻይና የአፍሪካ ሀገራትን የግብርናና የማምረቻ ዘርፍ ምርቶችን ወደ ሀገሯ በማስገባት የተጀመረውን እድገት እንዲቀጥል እንደምታደርግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ቤጅንግ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በጤና፣ በአረንጓዴ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች ተባብሮ የመስራት ፍላጎት አላት ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
ቻይና ከዚህም ባለፈም በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ካላት 10 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ለአፍሪካ ሀገራት ልትሰጥ ማሰቧንም ይፋ አድርጋለች፡፡