ሀገሪቱ በብድር ጫና ምክንያት እየተጎዱ ካሉ ሀገራት መካከል ዋነኛዋ ናት
ቻይና ለዚምባብዌ ብድር ሰረዘች።
ደቡብ አፍሪካዊቷ ሀገር ዚምባብዌ ከቻይና ከተበደረቻቸው ብድሮች ውስጥ የተወሰነው ተሰርዞላታል።
ቻይና የዚምባብዌን ብሔራዊ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ወለድ አልባ የሆኑ ብድሮችን ሰርዣለሁ ብላለች።
እስከ አሳለፍነው መስከረም ወር ድረስ ዚምባብዌ ያለባት ጠቅላላ ብድር መጠን 17 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር እዳ አለባት።
ከዚህ ብድር ውስጥ 12 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ያህሉ የውጭ ብድር ሲሆን ቀሪው ከሀገር ውስጥ ባንኮች የተወሰደ ብድር ነውም ተብሏል።
ቻይናም ዚምባብዌ ካለባት የብድር ጫና እንድታገግም በሚል ወለድ አልባ የሆኑ ብድሮችን እንደሰረዘች የሀገሪቱ ብዙሀን መገናኛዎች ዘግበዋል።
ዚምባብዌ በተጣሉባት ተደራራቢ ማዕቀቦች ምክንያት ከምዕራባዊያን ሀገራት እና ተቋማት
መበደር የማትችል ሲሆን አብዛኛውን ብድር ከቻይና እንደተበደረች ተገልጿል።
ዚምባብዌ ከቻይና ሶስት ቢሊዮን ዶላር እዳ እንዳለባት የተገለጸ ሲሆን ሀረሬ ያለባትን የብድር ጫና ቤጂንግ ማገዝ እንደምትፈልግ በዚምባብዌ የሀገሪቱ አምባሳደር ዙ ዲንግ ተናግረዋል።
ቻይና ለዚምባብዌ ከሰረዘችው ብድር ውስጥ ከፈረንጆቹ 2015 ወዲህ የወሰደቻቸው ናቸው የተባለ ሲሆን ለዚምባብዌ የሰረዘችው ብድር መጠን እስካሁን አልተጠቀሰም።
ቻይና በ2022 ለ17 የአፍሪካ ሀገራት 23 ወለድ አልባ ብድር አገልግሎት መስጠቷን አስታውቃለች።
ቻይና ለአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር በመስጠት የሀገራትን እጅ እየጠመዘዘች ነው የሚል ክስ እየቀረበባት ሲሆን ይህን ስሟን ለማደስ ወለድ አልባ ብድሮችን መስጠት ጀምራለች ተብላል።