ነርሶቹ አድማ የሚመቱት ወርሃዊ ደመወዛችን አንሶናል በሚል ነው
የዚምባብዌ ነርሶች የፊታችን ሰኞ አድማ እንደሚመቱ ገለጹ፡፡
የደቡባዊ አፍሪካዋ ዚምባብዌ ነርሶች የፊታችን ሰኞ ስራ አቁመው ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የሀገሪቱ የነርስ ሙያተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ሮበርት ችዱኩ ለሮይተርስ እንዳሉት እየተከፈላቸው ያለው ወርሃዊ ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ እና ይሄንን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ አስተላልፈናል ብለዋል፡፡
የዚምባብዌ መንግስት በተደጋጋሚ የነርሶችን ደመወዝ እንዲያስተካክል ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም የሚሉት ፕሬዝዳንቱ አሁንም ጥያቄያቸው እንዲመለስ ጥረት እንደሚያደርጉ አክለዋል፡፡
የዚምባብዌ አሁን ላይ ለአንድ የነርስ ሙያተኛ በወር 30 ሺህ የዚምባብዌ ዶላር ወይም 79 የአሜሪካ ዶላር (በዛሬ አርብ ሰኔ 10 ቀን 2014 ዓ/ም የምንዛሬ ዋጋ በብር ሲመነዘር 4 ሺ 94 ብር ከ96 ሳንቲም ማለት ነው) በመክፈል ላይ ሲሆን ይህም መሰረታዊ ወጪዎችን አይሸፍንም ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ሮበርት ገለጻ ከሆነ የሰኞው የነርሶች ሰላማዊ ሰልፍ አላማ መንግስት የተሸለ ደመወዝ እንዲከፍል ከመጠየቅ ባለፈ ምቹ የስራ አካባቢ እንዲፈጠር ለመጠየቅ ያለመ ነው፡፡
በመሆኑም የዚምባብዌ ዜጎች ሰኞ ነርሶች በስራ ገበታቸው ላይ እንደማይኖሩ በዕለቱን ለመንግስት በሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄያቸውን እንደሚያቀርቡ ተገልጿል፡፡
15 ሚሊዮን ገደማ የሕዝብ ብዛት ያላት ዚምባብዌ ወደብ አልባ ሀገር ስትሆን ግብርና እና ቱሪዝም የኢኮኖሚዋ ዋነኛ ገቢዎች ናቸው፡፡
ለእርሻ ስራ ምቹ የሆነ መልክዓ ምድር ያላት ዚምባብዌ ዛምቤዚ እና ሊምፖፖ ወንዞች ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ስራዎች አመቺ ቢሆንም በምዕራባዊያን ሀገራት በተጣለባት ማዕቀብ ኢኮኖሚዋ ተጎድቷል፡፡
በተደጋጋሚ በተጣለባት ማዕቀቦችም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በማጋጠሙ የምርቶች ዋጋ ግሽበቱ ከአፍሪካ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ዚምባብዌ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ ሲመሩ ከነበሩት ሮበርት ሙጋቤ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የተረከቡት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በመጣር ላይ መሆናቸውን በመናገር ላይ ናቸው፡፡