ዚምባብዌ ይህን የምታደርገው የገንዘቧ የመግዛት አቅም እጅግ መዳከሙን ተከትሎ ነው
ደቡብ አፍሪካዊቷ ዚምባብዌ በወርቅ ሳንቲሞች መገበያየት ልትጀምር ነው፡፡
የሃገሪቱ ብሔራዊ ባንክ የተዳከመውን የሃገሪቱን ገንዘብ የመግዛት አቅም ለመታደግ በሚል የወርቅ ገንዘቦችን ህጋዊ አድርጎ ማተም እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ለዶላርም አማራጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ነው በመጪው ሃምሌ 25 ወደ ገበያው ይገባል ያለው ባንኩ ያስታወቀው፡፡
ባሳለፍነው ወር በእጥፍ ጨምሮ የነበረው የዚምባብዌ የዋጋ ንረት 191 በመቶ ድረስ ስለማሻቀቡ ይነገራል፡፡ በዚህም የሃገሪቱ ዜጎች በከፋ የኑሮ ውድነት ውስጥ ነው የሚገኙት፡፡
የብሔራዊ ባንኩ ገዥ ጆን ማንጉዲያ የወርቅ ሳንቲሞቹ ገበያውን መቀላቀል በዜጎች ዘንድ ያለውን የአሜሪካን ዶላር ፍላጎት እንደሚቀንስ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የተሻለ የምንዛሬ ክምችትን ለመያዝ ከማስቻልም በላይ የሀገር ውስጥ መገበያያ ገንዘቦችን የምንዛሬ ዋጋ ከማሽቆልቆል ለመታደግ ትልቅ ዋጋ እንደሚኖረውም ገዢው ገልጸዋል፡፡
ማንጉዲያ "የወርቅ ሳንቲሞቹ በዓለም አቀፍ የወርቅ ዋጋ ላይ በመመስረት በተለያዩ የአገር ውስጥ ገንዘቦች እና በአሜሪካ ዶላር እንዲሁም በሌሎች የውጭ ምንዛሬ ገንዘቦዎች ጭምር ለሽያጭ እንደሚቀርቡም ነው የተናገሩት።
ሳንቲሞቹ ከባለ 22 ካራት ወርቅ ነው የሚዘጋጁት፡፡ ሳንቲሞቹን ለመለየት የሚያስችል ተከታታይ የቁጥር መለያ ኖሯቸው ይሰራሉም ተብሏል፡፡
በቀላሉ በአገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ለመገበያየት ወደሚያስችል ጥሬ ገንዘብ የሚቀየሩ ሆነው ይዘጋጃሉም ነው የተባለው። ለብድር እንደሚሆኑና የብድር ተቋማትም ዋስትና አድርገው ሊይዟቸው እንደሚችሉም ማንጉዲያ ተናግረዋል።