ቻይና ወንጀለኛን የሚለይ እና የሚያስቆም የሮቦት ፖሊስ አሰማራች
ክብ ቅርጽ ያለው ሮቦት በውሀ እና በየብስ ላይ ያለምንም ችግር መጓዝ የሚችል ነው ተብሏል

ሮቦቱ በተገጠመለት ካሜራ የጠፉ ወንጀለኞችን ፊታቸውን “ስካን” በማድረግ ብቻ በቀላሉ ማግኘት ይችላል ተብሏል
ቻይና ወንጀለኛን የሚለይ እና አሳዶ የሚይዝ አዲስ የሮቦት ፖሊስ ጥቅም ላይ አውላለች፡፡
አርቲ-ጂ የተባለው ክብ ቅርጽ ያለው ሮቦት የቻይና ሮቦቲክስ ኩባንያ የሆነው ሎጎን ቴክኖሎጂ ምርት ነው ተብሏል፡፡
ቴክኖሎጂው በአደገኛ አካባቢዎች እና ሁኔታዎች ውስጥ ፖሊሶችን ለመርዳት የሚያግዝ ሲሆን እስከ 4 ቶን ድረስ የጉዳት መጠንን መቋቋም እንደሚችል ተነግሮለታል፡፡
አርቲ-ጂ የተባለው በከፍተኛ የሰውሰራሽ አስተውሎት የበለጸገው ሮቦት በደረቅ መሬት፣ በጭቃ እና በውሀ ላይ ያለምንም ችግር የሚጓዝ ሲሆን በሰአት 35 ኪሎሜትር መሸፈን የሚችል ነው፡፡
ወንጀለኞችን መለየት እና እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ የሚችለው የጥበቃ ሮቦት ከሰሞኑ በከተሞች ላይ ከፖሊሶች ጎን ሲጓዝ የብዙ ሰዎችን ትኩረት ስቧል።
የፈጠራው ባለቤት ሎጎን ቴክኖሎጂ ስለአገልግሎቱ በሰጠው ማብራርያ ሮቦቱ በተለያዩ መንገዶች ወንጀልን መከላከል የሚችል ነው ብሏል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚንቀሳቀሱ ካሜራዎቹ በዙሪያቸው ያሉ ሁከቶችን ወይም ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን ለይተው ማወቅ ይችላሉ፤ የፊት መለያ ሶፍትዌሩ ደግሞ የጠፉ ወንጀለኞችን ፊታቸውን “ስካን” በማድረግ ብቻ በቀላሉ ማግኘት ይችላል።
ከዚያም ሌሎች ሮቦቶችን ወይም የሰው ህግ አስከባሪዎች እንዲደርሱለት ጥሪ በማስተላለፍ ተጠርጣሪዎችን በማሳደድ ገጭቶ በመጣል ወይም የተገጠመለትን የመረብ ሽጉጥ በመተኮስ ተፈላጊው ሰው እንዳይንቀሳቅስ አስሮ መያዝ የሚያስችል አቅም አለው፡፡
ሮቦቱ ለመጀመሪያ በሎጎን ቴክኖሎጂ ለዕይታ ከቀረበበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ግብረ መልሶችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
አንዳንዶች በተግባራዊ ሮቦቲክስ መስክ የቻይናን የበላይነት የሚያጠናክር የቴክኖሎጂ ግኝት በሚል ሲያሞካሹት ሌሎች ደግሞ ዲዛይኑ በእውናዊ ጦር ሜዳዎች ላይ እንዴት ሊያገለግል እንደሚችል በመጠይቅ አጣጥለውታል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቻይና ከተሞች ከህግ አስከባሪ አባላት ጎን ከተሞችን ሲቃኝ የተስተዋለው የሮቦት ፖሊስ በቋሚ አባልነት ይቀላቀል ወይም በሙከራ ደረጃ ይሰማራ ይፋዊ መረጃ አልተገለጸም፡፡