አድማጮችን አልሳባችሁም በሚል ጋዜጠኞቹን በማባረር ሮቦት ጋዜጠኛ የቀጠረው ሚዲያ
ከስራ የተባረሩት ጋዜጠኞች በኤአይ ተተካን ፍትህ ይስፈን ሲሉ ስሞታ አቅርበዋል
የፖላንዱ ክራኮው ሬዲዮ ጋዜጠኞቹን ካሰናበተ በኋላ የኤአይ ጋዜጠኞች ቀጥሯል
አድማጮችን አልሳባችሁም በሚል ጋዜጠኞቹን በማባረር ሮቦት ጋዜጠኛ የቀጠረው ሚዲያ
የፖላንዱ ክራኮው ሬዲዮ ለበርካታ ዓመታት በመደመጥ የሚታወቅ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ግን ተዘግቷል።
ሬዲዮ ጣቢያው የነበሩትን ጋዜጠኞች ካሰናበተ በኋላ የኤአይ ጋዜጠኞችን መቅጠሩን እና ዳግም ስርጭቴን ጀምሬያለሁ ብሏል።
ይህን ተከትሎ በኤአይ የተተኩት የቀድሞው ጋዜጠኞች ግፍ ተፈጽሞብናል ሲሉ ለሀገሪቱ መንግሥት ስሞታ አቅርበዋል።
ጉዳዩ በመላው ፖላንድ መነጋገሪያ መሆኑን ተከትሎ ሬዲዮ ጣቢያው ለምን ጋዜጠኞቹን እንዳሰናበቱ ተናግሯል።
እውነተኛ ጋዜጠኞቹ የአድማጮችን ቀልብ መሳብ ባለመቻላቸው ምክንያት ኤአይን ለመጠቀም ተገደናል ብሏል።
አዲሶቹ የኤአይ ጋዜጠኞች ወጣቶች ምን እንደሚፈልጉ እንዲያውቁ ተደርገው መልማታቸውንም ሬዲዮ ጣቢያው አስታውቋል።
የፖላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ድጅታል ጉዳዮች ሚንስትር ክሪዝስቶቭ ጋውኮውስኪ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ "እኔ የኤአይ ደጋፊ ነኝ ነገር ግን በኤአይ እና በሰው መካከል ያለው ድንበር መከበር አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
ኤአይን መቆጣጠሪያ ህግ ያስፈልጋል ያሉት ሚንስትሩ ጋዜጠኞቹ ያቀረቡት ስሞታ ትክክል መሆኑን እና ተገቢ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው ማለታቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ሚንስትሩ አክለውም ኤአይን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ገልጸው ነገር ግን ቴክኖሎጂው ሰዎችን ሊጎዳ በሚችልበት መልኩ ሊሆን አይገባም ሲሉም ተናግረዋል።
ሬዲዮ ጣቢያው በፖላንዳዊያን ተወዳጅ በሆኑት ገጣሚ ዊስላዋ ስዝምቦርስካን ድምጽ ተመሳስሎ የተሰራ ድምጽን የኤአይ ጋዜጠኞቹ እንዲጠቀም አድርጎ እያሰራጨ እንደሆነ ተገልጿል።