ኢኮኖሚ
የአሊባባ መስራች ጃክ ማ ከቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ "ጎብኝ ፕሮፌሰርነትን" ተቀበሉ
ጃክ ማ ምርምር ማማከር እና በአስተዳደርና ንግድ ዘርፍ እንደሚያስተምሩ ተነግሯል
አዲሱ ስራ ይፋ የሆነው ጃክ ማ ወደ ቻይና ከባህር ማዶ ቆይታ ባለፈው ወር ከተመለሱ በኋላ ነው
የአሊባባ ቡድን መስራች ጃክ ማ በቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ በሚተዳደረው ቶኪዮ ኮሌጅ ጎብኝ ፕሮፌሰር እንዲሆኑ መጋበዛቸውን ዩኒቨርሲቲው ተናግሯል።
የቻይና ታዋቂው ስራ ፈጣሪ የቅጥር ጊዜያቸው በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን፤ ነገርግን ውሉ በየዓመቱ የሚታደስ መሆኑን ዩኒቨርሲቲው ገልጿል።
በኮሌጁ ውስጥ ጃክ ማ በአስፈላጊ የምርምር ጭብጦች ላይ ማማከር እና በአስተዳደር እና ንግድ ትምህርቶችን በመስጠት እንደሚሰሩ ተነግሯል።
ይህ የተነገረው ጃክ ማ ወደ ቻይና ባለፈው መጋቢት ወር ከተመለሱ በኋላ ነው።
የቻይና የግል ንግዶች ከባድ የሁለት ዓመታት የቁጥጥር እርምጃን ተከትሎ የአሊባባ መስራች ከአንድ ዓመት በላይ የባህር ማዶ ቆይታ በኋላ ሀገራቸው መግባታቸው ይታወሳል።
ቶኪዮ ኮሌጅ የተመሰረተው በፈረንጆች 2019 በቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ፣ በውጭ ሀገር ተመራማሪዎች እና የምርምር ተቋማት መካከል መስተጋብር ሆኖ እንዲያገለግል በማለም መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።