ጃክ ማ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለአፍሪካ የለገሷቸው ቁሳቁሶች አዲስ አበባ ገቡ
ጃክ ማ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለአፍሪካ የለገሷቸው ቁሳቁሶች አዲስ አበባ ገቡ
የኢትዮጵ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የአሊባባ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዲሁም የጃክማ ፋውንዴሽን መስራች ሚስተር ጃክ ማ ባደረጉት ውይይት በአፍሪካ ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ባለሃብቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት ከጃክማ የተበረከቱትንና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግሉ ቁሳቆሶችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሃገራ እንድታከፋፍል ሃላፊነት የተሰጣት ሲሆን የሚሰራጩት ቁሳቁሶችም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ - ጃክ ማ ኢንሽዬቲቭ ብሔራዊ ኮሚቴ አስተባባሪ ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) እንደገለጹት ዛሬ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘው አዲስ አበባ የገቡት የመከላከያ ቁሳቁሶች ከሰኞ ጀምሮ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ይጓጓዛሉ ብለዋል፡፡
ለኢትዮጵያ እና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሚሰራጩት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ቁሳቁሶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ዛሬ አዲስ አበባ መግባታቸውን ያስታወቁት ዶ/ር ሹመቴ፣ ቁሳቁሶቹ የምርመራ ቁሶች እና የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን እንደሚያካትቱ ነው ያስታወቁት፡፡
ሁሉም ለሃገራቱ የሚሰራጩት እነዚህ ቁሳቁሶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚጓጓዙ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገ/ማሪያም የገለጹ ሲሆን አየር መንገዱ እነዚህን ቁሳቁሶች ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የሚያጓጉዘው በነጻ ነው ተብሏል፡፡
የብሔራዊ ኮሚቴው አስተባባሪ ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገ/ማሪያምና ሌሎችም ጃክ ማ እና ቻይና ትክክለኛውን የአብሮነትና የወገን ደራሽነት ሚናቸውን ተወጥተዋል ብለዋል፡፡
ለእያንዳንዱ የአፍሪካ ሃገር 20 ሺህ መመርመሪያዎች፣ 100 ሺህ የፊት ጭምብል፣ የህክምና ባለሙያዎች የሚለብሷቸው 1 ሺህ መከላከያ ልብሶች የሚከፋፈል ይሆናል።
ዛሬ ከገቡት ቁሳቁሶች የኢትዮጵያ ድርሻ በመላው ኢትዮጵያ እንዲሁም እንዲደርሳቸው ለታሰበላቸው የአፍሪካ ሀገራት እስከ ፊታችን ማክሰኞ ድረስ ተሰራጭተው ይጠናቀቃሉ ተብሏል።
ቀሪዎቹ ድጋፎችም በሚቀጥሉት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የሚጠናቀቁ ይሆናል።
የቁሳቁሶቹን መግባት አስመልክቶ በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ የጤና ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካዮችን ጨምሮ በርካቶች የተገኙ ሲሆን የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርን በመወከል በህብረቱና በኢትዮጵያ የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢድዋርድ ዞሊዛ ማካያ፣ በኢትዮጵያ የጅቡቲ አምባሳደር እና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋለ፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የአሊ ባባ መስራች እና ባለቤት ጃክ ማ የአፍሪካ ሃገራት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የሚውል ድጋፍ ለማድረግና ለማሰራጨት ኢንሽዬቲቩን ያቋቋሙት የዛሬ ሳምንት እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ድጋፉ ለ54 የአፍሪካ ሀገራት ቫይረሱን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የሚውል የህክምና ቁሳቁስ መሆኑንም ጃክ ማ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።