
ይህን አፈር መጠቀም ሀብታም ያደርጋል በሚል በርካቶች እየሸመቱት ይገኛሉ
ባለጸጋ ያደርጋል በሚል በ120 ዶላር እየተሸጠ ያለው አፈር
የዓለማችን ቁጥር ሁለት ሀብታም ሀገር በሆነችው ቻይና በአነስተኛ ካርቶን ወይም ከረጢት መሳይ እቃ መያዣ እየተሸጠ ያለው ነገር ብዙዎችን አስገርሟል።
ይህ እቃ ባንኮች ከተገነቡባቸው መሬት ላይ የተቆፈረ አፈር ሲሆን አንድ ከረጢት አፈር በ880 ዩዋን ወይም 120 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።
ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት እንደዘገበው ከሆነ ይህ ከባንኮች ህንጻ ስር ይወጣል የተባለው አፈር ሰዎችን ባለጸጋ ያደርጋል የሚል ዕምነት አሳድሯል።
በንግዳቸው እንዲሳካላቸው የፈለጉ ቻይናዊያን ይህን አፈር እየሸመቱ እንደሆነም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
አፈሩ በበይነ መረብ የንግድ አውታሮች አማካኝነት ለሽያጭ የቀረበ ሲሆን የአፈሩ ተፈላጊነት መጨመሩን ተከትሎ እስከ አንድ ሺህ ዩዋን ደርሷል ተብሏል።
ለሽያጭ የቀረበው ይህ አፈር ከአራት የቻይና ግዙፍ ባንኮች ማለትም ከቻይና ግብርና ባንክ፣ ከኢንዱስትሪ ባንክ ኦፍ ቻይና፣ ከንግብ ባንክ እና ከቻይና ኮንስትራክሽን ባንክ ህንጻዎች ስር የተቆፈረ እንደሆነ ተገልጿል።
የሀብት መጠንን ይጨምራል የተባለው ይህ አፈር ከንግድ እና ኢንቨስትመንት ጋር ያሉ መጥፎ ነገሮችን ያስወግዳል ተብሎም ይታመንበታል።
አፈር ሻጭ ነጋዴዎች አፈሩን በሌሊት ይቆፍራሉ የተባለ ሲሆን እንደተባለው ይህ አፈር የተባለውን ያህል ሀብት ያስገኛል የሚለው አመለካከት እስካሁን በሳይንስ አልተረጋገጠም።
በቅርቡ ተዓምረኛ የተባለውን አፈር የገዛ እና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ቻይናዊ እንዳለው ብዙ ጓደኞቹ አፈሩን እንደገዙ እና እንደተባለው አፈሩ ሀብት ካስገኘ በሚል እሱም እንደገዛ ተናግሯል።
ድርጊቱ በመላው ቻይና መነጋገሪያ የሆነ ሲሆን ብዙዎች ሰዎች አፈር ከመግዛት እንዲቆጠቡ እና ገንዘባቸውን እንዳይጭበረበሩ ሲሉ አሳስበዋል።