የአሜሪካ እና የቻይና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት ከአንድ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተነጋገሩ
አሜሪካ ይህ ውይይት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል የሚል ተስፋ አላት
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን የወታደራዊ መረጃ ልውውጥ ያቋረጠችው የቀድሞዋ የአሜሪካ አፈጉባኤ ቻይና ታይዋንን በመጎብኘታቸው ምክንያት ነበር
የአሜሪካ እና የቻይና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተነጋገሩ።
የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለስልጣናት እና የቻይና አቻቸው ከአንድ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የበይነ መረብ ውይይት ማድረጋቸውን ፔንታጎን(የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር) አስታውቋል።
አሜሪካ ይህ ውይይት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል የሚል ተስፋ እንዳላት ሮይተርስ ዘግቧል።
ስብሰባው የተደረገው ባለፈው ወር የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጅንፒንግ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለመመለስ መስማማታቸውን ተከትሎ ነው።
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያላትን የወታደራዊ መረጃ ልውውጥ ያቋረጠችው የቀድሞዋ የአሜሪካ አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ቻይና እንደ ራሷ ግዛት የምታያትን ታይዋንን በመጎብኘታቸው ምክንያት ነበር።
የጆይንት ችፍ ኦፍ ስታፍ ሊቀመንበር የሆኑት የአሜሪካ የአየር ኃይል ጀነራል ቻርለስ ኪው. ብራውን እና የቻይናው ሊብሬሽን አርሚው ጀነራል ሊዩ ዘንሊ "በበርካታ ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ጉዳዮች" ላይ መወያየታቸውን የብራውን ቢሮ ገልጿል።
ጀነራል ሊዩ የውጊያ ዘመቻ እና እቅድን የሚመለከተው ወታደራዊ ክፍል ኃላፊ ናቸው።
ፔንታጎን በሁለቱ ወታደራዊ ኃላፊዎች መካከል ያለው ውይይት በተሳሳተ ስሌት የሚደረግን ግጭት ለመከላከል ያስችላል ብሏል።
ጀነራል ብራውን ስለአብሮ መስራት አስፈላጊነት፣ ፉክክርን በአግባቡ ስለማስኬድ እና በተሳሳተ ስሌት ግጭት ውስጥ መግባትን ስለማስወገድ እና ቀጥተኛ የግንኙነን መስመርን ስለመዘርጋት ጉዳይ መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ከአንድ ወር በፊት ብራውን ከሊዩ ጋር ለመወያየት ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ደብዳቤ ልከው ነበር።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር እንደገለጸው ጀነራል ሊዩ የተረጋጋ እና ጤናማ ግንኙነት መመስረት ለሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ቁልፍ ነው ሲሉ ተናግረዋል።