ትዳር ያልመሰረቱ ሰራተኞቹ እንዲያገቡ ቀነ ገደብ ያስቀመጠው የቻይና ኩባንያ
ኩባንያው ከ28-58 አመት እድሜ ያላቸው ሰራተኞቹ እንዲያገቡ ባስቀመጠው አስገዳጅ ቀነ ገደብ ትችት ተሰንዝሮበታል

በተቀመጠው ቀነ ገድብ ትዳር የማይመሰርቱ ላጤዎች እና አግብተው የፈቱ ሰራተኞች ከስራቸው እንደሚባረሩ አስጠንቅቋል
ላጤ እና ከትዳራቸው የተፋቱ ሰራተኞቹ ትዳር እንዲመሰርቱ አስገዳጅ ቀነ ገደብ ያስቀመጠው የቻይናው የኬሚካል ኩባንያ መነጋገርያ ሆኗል፡፡
ድርጊቱን የፈጸመው በምስራቅ ቻይና ሻንዶንግ ግዛት የሚገኘው 1200 ሰራተኞች ያሉት የሹንቲያን ኬሚካል ማምረቻ ኩባንያ ነው፡፡
ኩባንያው ከ28 -58 አመት እድሜ ላይ የሚገኙ ያላገቡ እና አግብተው የፈቱ ሰራተኞቹ እስከመጪው መስከረም 30 ድረስ ትዳር የማይመሰርቱ ከሆነ ከስራቸው ሊፈናቀሉ እንደሚችሉ አሳስቧል፡፡
በተጨማሪም ሰራተኞቹ እስከ ሁለተኛው የፈረንጆቹ ሩብ አመት ድረስ ቤተሰብ መመሰረት የሚያስችል ሂደት ውስጥ እንዲገኙ አዟል፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነ በሶስተኛው ሩብ አመት ድርጅቱ በሚሰራው ግምገማ ቤተሰብ ያልመሰረተ ወይም ያላገባ ሰራተኛ ውል እንደሚቋረጥ ነው ያስታወቀው፡፡
ኩባንያው ይህን ያደረገው የወጣቶች ቁጥር መመናመን ያጋጠመው የቻይና መንግስት ልጆች እንዲወለዱ እና ወጣቶች ትዳር እንዲመሰርቱ የያዘውን ፖሊሲ ለመደገፍ ነው ብሏል፡፡
ሀገሪቱ ያጋጠማትን የውልደት ምጣኔ ለማሻሻል እና የስነ ህዝብ ፖሊሲዋን ለመከለስ በጀመረችው ጥረት በኮሌጆች ጭምር ስል ፍቅር ግንኙነት እና ትዳር ጠቀሜታ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ይሁንና የኬሚካል ኩባንያው ሰራተኞቹን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ትዳር እንዲገቡ ያወጣው አዲስ መመሪያ ከፍተኛ ትችት እና ተቃውሞን አስከትሎበታል፡፡
ከፍተኛ ቁጥር ህዝብ ባለቤት በሆነችው ቻይና የጡረታ መውጫ እድሜን ለማራዘም መንግስት በእንቅስቃሴ ላይ በሚገኝበት ሁኔታ ወጣቶች ስራ አግኝተው ትዳር ለመመስረት ሁኔታዎች ፈታኝ መሆናቸውን በቻይና ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ዜጎች ሀሳባቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
የአካባቢው የሰው ኃይል እና የማህበራዊ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊዎች የኬሚካል ኩባንያውን በየካቲት 13 ከጎበኙ በኋላ መመሪያው የቻይናን የሠራተኛ ሕግ የሚጥስ መሆኑን በመጠቆም እንዲሻር ማድረጋቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የቅርብ ጊዜ የመንግስት መረጃ እንደሚያሳየው በቻይና ውስጥ የአዲስ ተጋቢዎች ቁጥር ባለፈው አመት በአንድ አምስተኛ ቀንሷል፡፡