
ፈጣሪ አንዴ አትርፎኛል ዳግም ወደሰው ቤት አልገባም ያለው ይህ ሰው ሰው ሰራሽ ቤት አልኖርም ብሏል
ከመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ በጫካ የሚኖረው ሰው
ከሁለት ዓመት በፊት በቱርክ ባጋጠመ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት 50 ሺህ ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በደቡባዊ ቱርክ ባጋጠመው በዚህ አደጋ ምክንያት ከነቤተሰቡ በተዓምር የተረፈው አሊ ቦዞግላን አንዱ ነበር።
ይህ ሰው ይህን ሰቅጣጭ አደጋ ካየሁ በኋላ ዳግም ወደ መኖሪያ ቤት አልገባም ብሎ በጫካ ውስጥ እየኖረ ይገኛል።
በዋሻ ውስጥ ኑሮ ተመችቶኛል የሚለው ይህ ሰው እየኖረበት ያለው ዋሻ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎችን ተቋቁሞ ቆይቷል ብሏል።
የሶስት ልጆች አባት የሆነው አሊ ከእንግዲህ ሰው ሰራሽ ቤት ውስጥ የመኖር ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል።
ሚስት እና ልጆቹ እሱን ተከትለው ወደ ዋሻው የመምጣት ፍላጎት ስለሌላቸው ብቻውን በዋሻ ውስጥ እየኖረ መሆኑን ተናግሯል።
በዋሻ ውስጥ ለብቻ መኖር ከባድ ቢሆንም ደስተኛ ህይወት ስመራ ሁለት ዓመት ሆኖኛል ማለቱን የቱርኩ ሀበር ሚዲያ ዘግቧል።
ከሁለት ዓመት በፊት የካቲት ወር ላይ ያጋጠመው ይህ አደጋ ደቡባዊ ቱርክን እና ሰሜናዊ ሶሪያ አካባቢዎችን ጎድቷል።
ቱርክ በመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ደረጃውን ያልጠበቁ ህንጻዎች እንዲገነቡ አድርገዋል ያለቻቸውን ባለ ንብረቶች እና ባለሙያዎችን ማሰሯ ይታወሳል።
በ20 ዓመት ታሪክ ውስጥ በገዳይነቱ አንደኛ ነው የተባለው ይህ አደጋ ከ55 ሺህ በላይ ሶሪያዊያንን እና ቱርካዊያንን ገድሏል።