ትራምፕ የቢሊየነሩን መስክ እግር ሲስሙ የሚያሳይ "ዲፕ ፌክ" ቪዲዮ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ታየ
በቪዲዮው ውስጥ መስክ ባዶ እግሩን ወደ ኋላ ሲንጋለልና ትራምፕ ደግሞ በጉልበታቸው ተንበርክከው ሲስሙት ያሳያል

ቪዲዮው የታየበት የመንግስት መስሪያ ቤት ጉዳዩን አጣርቶ ድርጊቱን በፈጸሙት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል
ትራምፕ የቢሊየነሩን መስክ እግር ሲስሙ የሚያሳይ "ዲፕ ፌክ" ቪዲዮ በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ ታየ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቢሊየነሩን ኢለን መስክ እግር ሲስሙ የሚያሳይ 'ዲፕ ፌክ' ወይም ሀሰተኛ ቪዲዮ በቤቶችና ከተማ ልማት ዲፓርትመንት(ኤችዩዲ) መስሪያ ቤት ባሉ ስክሪኖች መታየቱ መነጋገሪያ ሆኗል።
ቪዲዮው ሲከፈት 'ሎንግ ሊቭ ዘ ኪንግ' ወይም እውነተኛው ንጉስ ረጅም እድሜ የሚል አጭር ጽሁፍ ተላልፏል። በቪዲዮው ውስጥ መስክ ባዶ እግሩን ወደ ኋላ ሲንጋለልና ትራምፕ ደግሞ በጉልበታቸው ተንበርክከው ሲስሙት ያሳያል።
በኤችዩዲ ካፍቴሪያ ባሉ ስክሬኖች እንዲታይ ተደርጓል የተባለው የዚህ ቪዲዮ ባለቤት እስካሁን አልታወቀም።
'ሎንግ ሊቭ ዘ ኪንግ' ከሚል አጭር ርዕስ ጋር የተለቀቀው ይህ ቪዲዮ ከቀናት በፊት ' ሎንግ ሊቭ ዘሪል ኪንግ' በማለት ትሩዝ በተባለው ገጻቸው ያሰፈሩት ትራምፕ ከመስክ ጋር ባላቸው ግንኙነት ላይ ለመሳለቅ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ(ኤአይ) የተቀነባበረ እንደሆነ በርካታ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ከፍቴሪያው ቪዲዮውን ያጫወተው ተጠልፎ ይሁን አስቦበት ገልጽ አልተደረገም።
የኤችዩዲ ቃል አቀባይ ካሲ ሎቬት "ይህ ሌላኛው የግብር ከፋዮች ዶላርና ሀብት ብክነት ነው፤ በድርጊቱ በተሳለፉት በሁሉም ላይ ተገቢ እርምጃ እንወስዳለን" ሲሉ መናገራቸው ኤንዲቲቪ ዘሂልን ጠቅሶ ዘግቧል።
ቢሊየነሩ ኢለን መስክ ፕሬዝደንት ትራምፕ ስልጣን ከያዙ ወዲህ በአሜሪካ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ጉልህ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕ መስክን የበጀትና የሰው ኃይል ቅነሳ የሚቆጣጠረውን የመንግስት ውጤታማነት ዲፓርትመንትን (ዶጅ) እንዲመራ ሾመውታል።
መስክ በቅርቡ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች ሳምንታዊ አፈጻጸማቸው እንዲያሳውቁት የኢሜል መልክት ከላከ በኋላ የፌደራል መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ሰራተኞች ምላሽ እንዳይሰጡ ማሳሰቢያ ሰጥተው ነበር።