"የፕሪሚየር ሊጉ አጭበርባሪ" ከአሜሪካ ለብሪታንያ ተላልፎ ተሰጥቶ ዳግም ዘብጥያ ወርዷል
ሜዲ አባሊምባ የተባለው የቀድሞ የክሪስታል ፓላስ እና ፉልሃም ተጫዋች ታዋቂ ሰዎችን በማታለል ተከሶ በተደጋጋሚ ታስሮ ነበር

ኔትፍሊክስ በ2023 በሰራው ዘገቢ ፊልም የአባሊምባን የማጭበርበር ስልት ማጋለጡ ይታወሳል
"የእግርኳሱ አአጭበርባሪ" የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ሜዲ አባሊምባ ዳግም ወደ ዘብጥያ መውረዱ ተነገረ።
የ35 አመቱ የቀድሞው እግርኳስ ተጫዋች የፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋች ነኝ እያለ ዝነኛ ሰዎችን ሲያጭበረብር ቆይቷል።
የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ ቴሪ ሆነሪ ሚስት የነበረችው ተዋናይት ክሌር ሜሪ እና "ሎቭ አይዝላንድ" በተሰኘው የአይቲቪ ሪያሊቲ ሾው ዝነኝነትን ያተረፈችው ጆርጂያ ስቲል የአባሊምባ ሰለባ ከሆኑ መካከል ይገኙበታል።
ወጣቱ የማጭበርበር መረቡ ውስጥ ያስገባቸውን ግለሰቦች በቅንጡ ሆቴሎች ውስጥ ቀጥሮ ይጋብዛቸዋል፤ በሄሊኮፕተር እና በአውሮፕላኖች ወደተለያዩ ሀገራት ይወስዳቸዋል። በቁጥጥሩ ስር እንዳስገባቸው ሲያረጋግጥ ወደዋናው ስራው ይገባል።
አባሊምባ ከቀድሞው የቴሪ ሆነሪ ሚስት ክሌር ሜሪ 50 ሺህ ፓውንድ፤ ከጆርጂያ ስቲል ደግሞ 13 ሺህ ፓውንድ ማጭበርበሩን ኔትፍሊክስ "የእግርኳሱ አጭበርባሪ (ስካመር)" በሚል ርዕስ በሰራው ዘጋቢ ፊልም ላይ ራሳቸው ሰለባዎቹ ተናግረዋል።
አባሊምባ ማን ነው?
ሜዲ አባሊምባ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ነው የተወለደው። በልጅነቱ ወደ ብሪታንያ የገባው አባሊባማ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው በደርቢ ካውንቲ አካዳሚ ነው።
ክሪስታል ፓላስ እና ፉልሃምን ለበርካታ የእኝግሊዝ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን፥ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ሊቨርፑል እና ማንቸስተር ሲቲን ለመቀላቀልም ሙከራ አድርጎ ነበር።
አባሊምባ የእግርኳስ ህይወቱ በፈርንጆቹ 2012 ከተጠናቀቀ በኋላ ነው ወደ ማጭበርበር የገባው። ዋነኛ የማጭበርብሪያ ስልቱም የቀድሞው የቼልሲ ተጫዋች ጋይል ካኩታ ነኝ የሚል እንደነበር ተዘግቧል።
የቀድሞው ተጫዋች በፈረንጆቹ 2013 ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰሰበት የማጭበርበር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቶ በስድስት ወራት እስራት ቢቀጣም አልታረመም ይላል የስካይ ኒውስ ዘገባ።
የታክሲ ኩባንያን 10 ሺህ ፓውንድ በመመንተፍ፣ ክሎይ ሄንሪ የተባለች ሞዴልን የአሜሪካ ባህር ሃይል አመራር ነኝ በማለት 160 ሺህ ፓውንድ በማጭበርበርና በሌሎች ክሶች የአራት አመት ከሁለት ወራት እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበት ነበር።
ይሁን እንጂ በ2023 የእስር ጊዜው ሳይጠናቀቅ የተፈታው አባሊምባ ከብሪታንያ እንዳይወጣ የተላለፈበትን ውሳኔ ጥሶ ወደ አሜሪካ ተጉዟል።
የደርቢሻየር ፖሊስም ከአሜሪካ የደህንነት አካላት ጋር በመተባበር "ሚቺ ጆርዳን" በሚል ስሙን ለውጦ አሜሪካ የገባው "የፕሪሚየር ሊጉ አጭበርባሪ" አሜሪካውያንንም ኢላማ ማድረግ ሳይጀምር እንዲያዝ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በጥር 28 2025 በቁጥጥር ስር ውሏል።
ከሰሞኑም ለብሪታንያ ተላልፎ ተሰጥቶ የታሰረ ሲሆን፥ እስከ ጥቅምት 2026 በማረሚያ ቤት ይቆያል ተብሏል።