ከነጭ አባትና እናት የተወለደው ጥቁር ልጅ የ”አባቱ ማን ነው?” ጥያቄ አስነሳ
ቻይናዊው ወጣት ባለቤቱ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ልጅ መውለዷን እንዳወቀ ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል
ክስተቱ የቻይናውን ዌቦ ድረገጽ ተጠቃሚዎች በሁለት ጎራ ከፍሎ እያከራከረ ነው
ቻይናዊቷ ወጣት ዘጠኝ ወር የጠበቀችውንና በህይወቷ አስደሳች የሆነውን ቀን አጣጥማው ሳትጨርስ አስከፊ ነገር ገጥሟታል።
የወለደችው ልጅ ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው መሆኑ ባለቤቷን ጥርጣሬ ውስጥ ከቷል።
ከሁለት ነጭ ባልና ሚስቶች እንዴት ጥቁር ልጅ ይወለዳል ያለው አባት በርግጥም አባቱ እርሱ እንደሆነ ለማረጋገጥ ምርመራ ማድረግ አለብን ብሏል።
ቻይና ታይምስ ስሟን ያልጠቀሳትን የ30 አመት የሻንጋይ ከተማ ነዋሪ እናትን ታሪክ አጋርቷል።
በቀዶ ጥገና የወለደችው እናት ባለቤቷ እንደርሷ ሁሉ በጉጉት የሚጠብቀውን ልጅ ሲመለከት አይኑን ማመን አቅቶት ሊታቀፈው እንኳን እንዳልፈለገ ተናግራለች።
“ወደ አፍሪካ ተጉዤ አላውቅም፤ ጥቁር ቆዳ ቀለም ያለው ሰው ጋርም ተገናኝቼ አላውቅም” የምትለው ቻይናዊት ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ልጅ በመውለዷ ራሷም መጀመሪያ ላይ መደንገጧን አልሸሸገችም።
ከባለቤቷ የቀረበላትን የአባትነት ምርመራ ይደረግ ጥያቄ ተቀብላው እንደነበር የገለጸችው እናት፥ የልጄ አባት ከባለቤቴ ውጭ እንደማይሆን እርግጠኛ ነኝ፤ ምርመራው ግን የተበጠሰውን እምነታችን አይመልሰውም ብላለች።
አሁን ላይ ምርመራውን ማድረግ አለብኝ ወይ? እንዲህ አይነት ክስተትስ አጋጥሞ ያውቃል ወይ በሚል በዌቦ ድረገጽ ላይ ያቀረበችው ጥያቄም መነጋገሪ ሆኗል።
አስተያየት ሰጪዎች በሁለት ጎራ ተከፍለዋል፤ የልጁ ቆዳ ቀለም መጥቆር የእናትየዋን መወስለት ያጋለጠ ነው የሚሉት በአንድ ወገን ክስተቱ ተፈጥሯዊና በሂደት ሊስተካከል የሚችል ነው በሚል የሚከራከሩ ደግሞ በሌላ።
“መሰል ክስተት የሚፈጠረው የህጻናቱ የቆዳ ህዋሳት ሲቀጥኑና የደም ዝውውርን በሚገባ እንዳያካሂድ ሲያደርግ ነው” ያለ አንድ ባለሙያ መሆኑን የጠቀሰ አስተያየት ሰጪ፥ የህጻኑ የቆዳ ቀለም በሂደት እንደሚነጣ ተናግሯል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ አባት አራስ ሚስቱን የአባትነት ምርመራ መጠየቁ ምን ያህል የሞራል ስብራት እንዳለው በውል አልተረዳውም፤ ምርመራው አባትነቱን ቢያረጋግጥላትም ትዳራቸው በሰላም የመቀጠሉ ነገር ያበቃለት ይመስላል ማለታቸውን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።