የሚስቱን ውስልትና በሰርጉ እለት ያጋለጠው ሙሽራ
ሙሽራው፣ አንደኛ ሚዜው እና ሚስቱ ሲማግጡ የሚያሳየውን ፎቶ በሰርጋቸው እለት ወዳጅ ዘመድ እንዲመለከተው አድርጓል
በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሰፊ ትኩረት የተሰጠው የሙሽራው ድርጊት “የአመቱ ጣፋጭ በቀል” የሚል ስያሜ አግኝቷል
የሚስቱን ውስልትና በሰርጉ እለት ያጋለጠው ሙሽራ አነጋጋሪ ሆኗል።
በአዲሷ ሚስቱ ውስልትና በእጅጉ ልቡ ያዘነው ሙሽራ ተመጣጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ትክክለኛውን ጊዜ ሲጠባበቅ ሰንብቷል፡፡
የሰርግ ስነስርአቱን ለማከናወን ሳምንት ሲቀረው እጮኛው ከአንደኛ ሚዜው ጋር እንደምትማግጥ ያወቀው ባል ጉዳዩን ከጓደኛውም ጋር ሆነ ከእጮኛው ጋር ሊነጋገርበት አልፈቀደም፡፡
ሰርጉ ተደግሶ ባል እና ሚስቱ ቃለ መሀላ ለመፈጸም እየተዘጋጁ ባሉበት ቃል ከመግባቱ በፊት መናገር የሚፈልገው ነገር እንዳለ በመግለጽ ማይካራፎን ይቀበላል። ቀጥሎም በፖስታ የታሸገ ወረቀት ለሁሉም የሰርጉ ታዳሚዎች እንዲሰራጭ እና እንዲከፍቱት ያደርጋል፡፡
የታሸገው ፖስታ ውስጥ ሚስቱ ለመሆን ካጠገቡ የቆመችው ሴት እና አንደኛ ሚዜው ሲማግጡ የሚያሳይ ፎቶ ይገኝ ነበር፡፡
ሙሽራው “በፎቶው ላይ የምትመለከቱት ምስል ውዷ እጮኛየ እና የልብ ጓደኛየ ከጀርባየ ሲማግጡ የሚያሳይ ነው ከእንደዚች አይነት ሴት ጋር ትዳር ባልመሰርት የሚፈርድብኝ ያለ አይመስለኝም” ካለ በኋላ ሙሽሪት በድንጋጤ በቆመችበት ከቤተሰቦቹ ጋር የሰርጉን አዳራሽ ጥሎ ወጥቷል፡፡
የሚስቱን መማገጥ ያወቁት የሙሽራው ቤተሰቦች ስለሁኔታው ካወቁ በኋላ በምን አይነት መንገድ ሊበቀላት እንዳሰበ ሲነግራቸው በሀሳቡ ተስማምተው ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል በሰርግ ስነስርአቱ ላይ ታድመዋል፡፡
በዚህ የተነሳም የሰርግ ፕሮግራሙን ሙሉ ወጪ ሙሽሪት እና ቤተሰቦቿ እንዲሸፍኑ ተገደዋል ሲል ደይሊ ሜል አስነብቧል፡፡
ጉዳዩን ወደ መገናኛ ብዙሀን የወሰደችው ሰርጉን ስታስተባብር የነበረችው ጆርጂያና የተባለች ግለሰብ ስትሆን በአንድ ፖድካስት ላይ ቀርባ ስለሁኔታው የተናገረችበት ቪድዮ በቲክቶክ ላይ ከአንድ ሚሊየን በላይ እይታ አግኝቷል፡፡
ጉዳዩን ተከትሎ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ሙሽራውን ጀግና ሲሉ የገለጹት ሲሆን ቃል አባዮችን የሚያስተምር ትክክለኛ ቅጣት ነው በሚል ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ሲቀጥሉ በሁለት በሚወዳቸው ሰዎች የተካደው ሙሽራ ህመም ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት ቀላል ነው፤ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ግን ይህን አይነት የበቀል እርምጃ እቅድ ማቀዱ የሚያስገርም ነው ብለዋል፡፡ በዚህም የአመቱ ጣፋጭ በቀል ሲሉ ሁኔታውን ገልጸውታል፡፡
ሌሎች ደግም ለትዳር የሚያስባትን ሴት ከልቡ የሚያፈቅራት ከሆነ በቤተሰቦች እና በወዳጆቿ ፊት በዚህ ልክ ማዋረዱ ተገቢ አይደለም በማለት ድርጉቱን ተቃውመዋል፡፡