የልጁን ፍቅረኛ የነጠቀው አባት በባንክ ሃላፊነት ላይ በነበረበት ጊዜ በሰራው የሙስና ወንጀል በቁጥጥር ስር ውሏል
የቀድሞ የባንክ ኦፍ ቻይና ሊቀመንበር የነበረው የ63 አመቱ ሊዩ ሊያንግ ለወጣት ሴቶች በሚያሳየው መማረክ አካባቢው ባሉ ሰዎች እና በጓደኞቹ ይታወቃል፡፡
የመጀመሪያ የትዳር አጋሩን ከፈታ በኋላ ከሶስት የተለያዩ ሴቶች ጋር ትዳር መስርቶ የነበረ ቢሆንም ሚስት የማይበረክትለት ግለሰቡ ከሁሉም ጋር ፍቺ ፈጽሟል፡፡
ግለሰቡ በየጊዜው አግብቶ የሚፈታው ለወጣት ሴቶች ካለው ፍቅር ጋር እንደሚያያዝ የሚጠቅሰው ኦዲቲ ሴንትራል ሁሉም ሴቶች ሊያንግ ከሚገኝበት እድሜ ጋር የማይቀራረቡ ወጣቶች መሆናቸውን ዘግቧል፡፡
በወጣት ሴቶች ከመጠን በላይ መሳቡ ለማንም የተደበቀ ባይሆንም የልጁን እጮኛ እስከመቀማት ያደርሰዋል ብሎ የገመተ ግን አልነበረም፡፡
አንድ ቀን ሊያንግ በቤት ውስጥ በተቀመጠበት ልጁ ከአንድ ወጣት ሴት ጋር ጎራ በማለት ትዳር ለመመስረት የወሰነባት እጮኛው መሆኗን ነግሮት ከአባቱ ጋር ያስተዋውቃቸዋል፡፡
በዚሁ ቅጽበት በልጁ እጮኛ የተማረከው አባት ጥንዶቹን ሰለሚለያይበት እና ልጅቷን የራሱ ስለሚያደርግበት እቅድ መወጠን ይጀምራል፡፡
ከትውውቁ ጥቂት ቀናት በኋላ ልጁ ያስተዋወቀው ሴት እጮኛው ልትሆን እንደማትችል በልጁ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተያያዘው፡፡
የልጅቷ ቤተሰቦች ጥሩ ሰዎች ስላልሆኑ ለልጁ እንደማትገባው በመንገርም ልጁን ለማሳመን ጥረት ማድረጉን ቀጠለ፡፡
ከአባቱ በተደጋጋሚ የሚቀርብብት የአትሆንህም ውትወታ የበረታበት ልጅ በመጨረሻም ከእጮኛው ጋር ያለውን ግንኙነት ለማቋረጥ ይወስናል፡፡
በዚህ እቅዱ የተሳካላት አባት የልጁን የቀድሞ ፍቅረኛ አድራሻ በማፈላለግ ውድ ስጦታዎችን እና ጌጣጌጦችን በመላክ ትኩረቷን ማግኝት ቻለ፤ በጊዜ ሂደትም በትዳር ለመጣመር ይስማማሉ፡፡
አባት አዲስ በጀመረው የፍቅር ግንኙነት ላይ ልጁ እንቅፋት እንዳይሆንበት ከአንድ ጓደኛው ልጅ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዲጀምሩ በማድረግ ትኩረቱን ለማስቀየር ሞክሯል፡፡
ከእጮኛው ጋር ከተለያየ ከስድስት ወራት በኋላ የቀድሞ ፍቅረኛው በቅርቡ ሶስተኛ የእንጀራ እናቱ እንደምትሆን የተረዳው ልጅ በድንጋጤ በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገብቷል፡፡
ከዜናው አስደንጋጭነት የተነሳም በአንድ ወቅት ህመሙ ተባብሶ ሆስፒታል ተኝቶ እንዲታከም ተገዷል፡፡
ከልጁ የቀድሞ እጮኛ ጋር ትዳር የመሰረተው ሊዩ ሊያንግ በባንክ ሃላፊነት ላይ በነበረበት ጊዜ በሰራው የሙስና ወንጀል በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ለአራተኛ ጊዜ የመሰረተው ትዳር እንዲፈርስ ምክንያት ሆኗል፡፡
በባንክ ኦፍ ቻይና በነበረው የሊቀመንበር ሀላፊነት 3.32 ቢሊየን የን (450 ሚሊየን ዶላር) ህገ ወጥ ብድር በመፍቀድ በቀረበበት ክስ በፍርድ ቤት ሂደት ላይ ይገኛል፡፡