አሳድጋ ለልጇ ሚስት ለማድረግ የ11 አመት ታዳጊ የጠለፈችው ቻይናዊ ዘብጥያ ወረደች
እናት በጉዋንዡ ግዛት ጉብኝት ስታደርግ የተመለከተቻት ታዳጊ ለልጇ “ምርጥ ሚስት” እንደምትሆን አምና ነው ከልጇ ጋር ጠለፋውን ያካሄደችው
ጠለፋውን ያደረጉት እናትና ልጅ የተላለፈባቸው የእስር ቅጣት አነስተኛ መሆን ግን ቅሬታ አስነስቷል
በቻይና ለልጇ ጥሩ ሚስት እንደምትሆን ያመነችባትን የ11 አመት ታዳጊ የተለፈችው እናት በእስራት ተቀጣች።
ያንግ የተባለችው እናት በጉዋንዡ ግዛት ሊፓንሹ በተባለች ከተማ ከ27 አመት ወጣት ልጇ ጉብኝት ስታደርግ ነው ለልጇ ሁነኛ ውሃ አጣጭ ትሆናለች ያለቻትን ታዳጊ የተመለከተቻት።
የታዳጊዋን ወላጆች ልጃቸውን ለልጇ ማጨቷን በመግለጽ ወደሚኖሩበት ኩሺንግ ከተማ ይዘዋት እንዲመጡም ትጠይቃለች።
የ11 አመቷ ታዳጊ አባት ግን የጋብቻ ጥያቄውን ውድቅ ያደርጉታል።
እናም እናት ከ27 አመት ልጇ ጋር ታዳጊዋን ለመጥለፍ በመምከር በቤቷ ብቻዋን የምትሆንበትን ጊዜ ጠብቀው ጠልፈው ወደሚኖሩበት ከተማ ይወስዷታል።
ታዳጊዋ ከተጠለፈች ከስድስት ቀናት በኋላ ግን ፖሊስ ጠላፊዎቹን በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ነው ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበው።
እናትና ልጅ ፍርድ ቤት ቀርበውም ለፈጸሙት የጠለፋ ወንጀል በእስራጥ እንዲቀጡ ተወስኖባቸዋል፤ ያንግ በሁለት አመት፤ ስሙ ያልተጠቀሰው ልጃቸው ደግሞ በሰባት ወር እንዲቀጡ ነው የተፈረደባቸው።
የፍርድቤቱን ውሳኔ ይግባኝ ያሉት እናትና ልጅ ውሳኔው ቢጸናባቸውም የተላለፈባቸው ቅጣት ጠለፋን የሚያበረታታ ነው ያሉ ቻይናውያን በማህበራዊ ሚዲያዎች ቅሬታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
“ህጻናትን የጠለፉ አካላትን በሰባት ወር መቅጣት ከባዱን ወንጀል ግፉበት እንደማለት ነው” ነው የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።
ቻይና በፈረንጆቹ 1950 ከ18 አመት በታች የሆኑ ህጻናትን ማግባት እና መጥለፍ በህግ ብትከለክልም በገጠራማ አካባቢዎች ለልጆቻቸው የወደፊት ሚስት ትሆናለች ብለው ያመኑባትን ታዳጊ የሚያሳድጉ ወላጆች እንዳሉ ነው የሚነገረው።