ተከስክሶ መኖሪያ ቤት ላይ ያረፈው የቻይና ተዋጊ ጄት ሰው ገደለ
ተዋጊ ጄቱ በሶቪዬት ህብረት ዘመን ከተመረቱ የሚግ-23 ተዋጊ አውሮፕላኖች መካከል መሆኑ ተነግሯል
በአደጋው በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውም ተነግሯል
በልምምድ ላይ የነበረ የቻይና ተዋጊ ጄት ተከስክሶ መኖሪያ ቤት ላይ ማረፉን ተከትሎ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ፡፡
በአደጋው በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውም ተነግሯል፡፡
ተዋጊ ጄቱ ዛሬ ጠዋት በማዕከላዊ ቻይና ሁቤይ ግዛት ከሚገኝ አንድ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ መከስከሱን የዘገበው ሲሲቲቪ አብራሪው የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ከአደጋው ተርፏል ብሏል፡፡
ተዋጊ ጄቱ በሶቪዬት ህብረት ዘመን ከተመረቱ የሚግ-23 ተዋጊ አውሮፕላኖች መካከል መሆኑ ተነግሯል፡፡ ይህም ጄቱ የአገልግሎት ዘመኑ ማብቂያ ላይ ይገኝ እንደነበር የሚያሳይ ነው እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፡፡
በቻይና ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ተደጋጋሚ የአውሮፕላን አደጋዎች እያጋጠሙ ነው፡፡ በቅርቡ አንድ የኢስተርን ላይንስ የመንገደኞች አውሮፕላን ተከስክሶ ጭኗቸው የነበሩ 132 ሰዎች በሙሉ ሞተዋል፡፡
ከወር በፊት በደቡብ ምዕራባዊ ቻይና ቾንግኪንግ ከተማ የተነሳና 122 ሰዎችን የጫነ የቲቤት አየር መንገድ አውሮፕላን የእሳት አደጋ ደርሶበት እንደነበር ይታወሳል፤ ምንም እነኳን በአደጋው የደረሰ ሰብዓዊ ጉዳት ባይኖርም፡፡
ቻይና “ሉዓላዊነቴን እና ደህንነቴን አደጋ ላይ የሚጥል እቅስቃሴ እያደረገች ነው” በሚል ከሰሞኑ ወደ አየርና የውሃ ክልሏ የቀረቡ የአውስትራሊያ የጦር አውሮፕላኖችን በረራ ማቋረጧ ይታወሳል፡፡