ቻይና አውስትራሊያ ከጠብ አጫሪ ድርጊቶቿ እንድትቆጠብ አስጠነቀቀች
ቻይና “የአውስትራሊያ የጦር አውሮፕላኖች ሉአላዊነቴና ደህንነቴ ላይ አደጋ የሚደቅን እቅስቃሴ እያደረጉ ነው” ብላለች
“አውስትራሊያ ከተግባሯ ካልተቆጠበች ከባድ መዘዝ ይዞባት ይመጣል” ስትልም ቻይና ዝታለች
ቻይና፤ አውስትራሊያ በአየር እና የውሃ ክልሏ አካባቢ ከምታደርገው ጠብ አጫሪ ድርጊት እንድትቆጠብ አሳሰበች።
“አውስትራሊያ የባህር ኃይል እና የአየር ሃይሎችን ድርጊቶች በጥብቅ ልትቆጣጠር ይገባል” ያለችው ቻይና፤ “ካልሆነ ግን የአውስትራሊያ ድርጊት ከባድ መዘዝን ይዞ ይመጣል” ስትል አስጠንቅቃለች።
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ታን ኬፌይ፤ የአውስትራሊያ 8A ASW የጦር የስለላ አውሮፕላን በዚሻ ደሴት አቅራቢያ በተደጋጋሚ ወደ ቻይና የአየር ክልል ቀርቦ መብረሩን ተከትሎ መግለጫ መስጠታቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ቃል አቀባዩ ታን ኬፌይ በመግለጫቸው፤ የቻይና ጦር የአውስትራሊያ የጦር አውሮፕላኖች መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተናግረዋል።
የአውስትራሊያ የጦር አውሮፕላን የቻይናን ሉዓላዊነት እና ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ የቻይና ጦር ለዚህ የሚሰጠው ምላሽ ምክንያታዊ እና ህጋዊ ይሆናል ሲሉም ተደምጠዋል።
አውስትራሊያ በትናትናው እለት “የቻይናዊ ተዋጊ ጄት አብራሪ 8A ASW የጦር አውሮፕላኗ አቅራቢያ አደገኛ እንቅስቃሴ አድርጓል” ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
የቻይናው ተዋጊ ጄት በአውስትራሊያ 8A ASW የጦር አውሮፕላን ላይ ፀረ-ራዳር መሳሪያ ጨምሮ ትንንሽ የአሉሚኒየም ቁርጥራጮችን የለቀቀ ሲሆን፤ እነዚህም የአውስትራሊያ አውሮፕላን ሞተር ውስጥ በመግባት በረራውን ለማቋረጥ እንዲገደድ አድርጓል።
8A ASW የሮያል አውስትራሊያ አየር ሃይል የባህር ላይ የስለላ አውሮፕላኖች ባሳለፍነው ግንቦት 18 ነበር በቻይና ጄ-16 ተዋጊ ጄቶች የማደናቀፍ ተግባር የተፈፀመው።
ቻይና የአውስትራሊያ አውሮፕላን ላይ እርምጃ የፈፀመችበትን ስፍራ ጨምሮ አብዛኛውን የቀጠናውን አካባቢዎች የራሷ ግዛት እንደሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።