ሩሲያና ቻይና በዚህ ሳምንት የጋራ የባህር ኃይል ልምምድ ሊያደርጉ ነው
የልምምዱ ዓላማ በሩሲያና ቻይና መካከል ያለውን የባህር ኃይል ትብብር ለማጠናከር መሆኑ ተነግሯል
ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በየዓመቱ ይካሄዳል የተባለው የጋራ የባህር ኃይል ልምምድ የፊታችን ረቡዕ ይጀምራል ተብሏል
ሩሲያ እና ቻይና ከፈረንጆቹ ታህሳስ 21 እስከ 27 ባለው ጊዜ ውስጥ የጋራ የባህር ኃይል ልምምዶችን እንደሚያደርጉ የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር አስታውቋል።
ከ2012 ጀምሮ በየዓመቱ የሚካሄደው የጋራ የባህር ኃይል ልምምዱ በምስራቅ ቻይና ባህር ላይ የሚሳይል እና መድፍን ጨምሮ እንደሚካሄድ የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ገልጿል።
"የልምምዱ ዋና ዓላማ በሩሲያ እና በቻይና መካከል ያለውን የባህር ኃይል ትብብር ለማጠናከር እና በእስያ ፓስፊክ ክልል ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅ ነው" ብሏል።
በየካቲት ወር ከተቀሰቀሰው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በኋላ ሞስኮ ከቤጂንግ ጋር ያላትን ፖለቲካዊ፣ ደህንነት እና ምጣኔ-ሀብታዊ ግንኙነቷን ለማሳደግ እየጣረች ነው ያለው ሮይተርስ፤ የቻይናውን መሪ ዢ ጂንፒንግን በጸረ-ምዕራብ ህብረት ውስጥ ቁልፍ አጋር አድርጋ ትመለከታለችም ብሏል።
ሞስኮ በየካቲት ወር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ትልቁን የመሬት ወረራ ከመጀመሯ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሁለቱ ሀገራት “ምንም ገደብ የለሽ” ስልታዊ አጋርነት የተፈራረሙ ቢሆንም ቤጂንግ ግን ሩሲያ በዩክሬን የምትወስደው እርምጃ እንዳሳሰባት ገልጻለች።
ሩሲያ አራት መርከቦቿ በልምምዱ ላይ እንደሚሳተፉ ገልጻለች። ሞስኮ ሚሳይል ተሸካሚ መርከቧን
ጨምሮ የልምምዱ አካል ናቸው ያለች ሲሆን፤ ስድስት የቻይና መርከቦች ከሁሉም ወገኖች አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ይሳተፋሉ ተብሏል።
የፊታችን ረቡዕ በሚጀመረው ልምምዱ ላይ ለመሳተፍ የሩሲያ መርከቦች ሰኞ እለት ከሩቅ ምስራቅ የቭላዲቮስቶክ ወደብ እንደተነሱ ተነግሯል።