በቻይና የተሰራው “ተንሳፋፊ የአየር ላይ መርከብ” የአለም ክብረ ወሰን የሆነ ከፍታ ላይ መብረሩ ተገለፀ
“ተንሳፋፊው መርከብ” ከመሬት በ9 ሺህ 32 ሜትር ከፍታ ላይ በመብረር አዲስ ክብረወሰን አስመዝግቧል
“ጂሙ ቁጥር 1” የሚል መጠሪያ ያለው የአየር ላይ መርከቡ በሰከንድ 30 ሜትር የሚጓዝ መሆኑ ተነግሯል
በቻይና የተሰራው “ተንሳፋፊ የአየር ላይ መርከብ” የአለም ክብረ ወሰን የሆነ ከፍታ ላይ መብረር መቻሉ ተገለፀ።
“ተንሳፋፊ የአየር ላይ መርከብ” ከመሬት 9 ሺህ 32 ሜትር ከፍታ ላይ በመንሳፈፍ አዲስ የዓለም የከፍታ ክብረ ወሰንን መስበር መቻሉንም ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
“ጂሙ ቁጥር 1” የሚል መጠሪያ ያለው ተንሳፋፊው መርከብ ሂሊየም በተሰኘ ጋዝ ተሞልቶ በአየር ላይ በሰከንድ 30 ሜትር በመብረር የሚችል መሆኑም ነው የተገለፀው።
ተንሳፋፊው መርከብ ባለፍነው እሁድ በቤጂንግ ሰዓት ከቀኑ 7 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ላይ 4 ሺህ 300 ሜትር ከፍታ ካለው ኮሞላግማ ተራራ ላይ ከሚገኘው የምርምር ጣቢያ መነሳቱ ተነግሯል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ላይም ተንሳፋፊው መርከብ የተራራው ከፍተኛ ጫፍ ከሆነው ከ8 ሺህ 840 ሜትር በላይ በማለፍ በ9 ሺህ 32 ሜትር ከፍታ ላይ በመብረር ነው አዲስ የዓለም የከፍታ ክብረ ወስን መስበር የቻለው።
2 ሺህ 625 ቶን የሚመዝነው ተንሳፋፊ የአየር መርከብ 9 ሺህ 60 ኩቢክ ሜትር የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፤ በተንሳፋፊው መርከብ ላይ የተገጠመው ተሸከርካሪም 90 ቶን የሚመዝን ነው ተብሏል።
ለአየር ሁኔታ ቅኝት ጥቅም ላይ ይውላል የተባለው ተንሳፋፊው መርከብ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የንጥረ ነገሮች ሁኔታ መረጃ መሰብሰብ እና የውሃ ትነት ሂደትን የሚከታተል ነው ተብሏል።
በቻይና ተንሳፋፊ የአየር ላይ መርከብ ስራ ላይ 64 አባላት ያለበት የባለሙያዎች ቡድን እንደተሳተፈበት የተነገረ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ “የቻይና 2020 የምድር ተልእኮ ጉባዔ” አካል መሆኑ ተመላቷል።