የ70 ዓመቱ አዛውንት “የዕድሜዬ መግፋት ከትምህርት ፍላጎቴ አላስቀረኝም” ብለዋል
የተለለያዩ የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዛሬው እለት ተማሪዎቻውን አስመርቀዋል።
ተማሪዎቻቸውን ካስመረቁት የትምህርት ተቋማት ውስጥ አንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ ናቸው።
በዛሬው እለት ከተካሄዱ ምርቃቶች ውስጥ ከወደ ቡሌ ሆራ የተሰማው የምርቃት ዜና የበርካቶችን ቀልብ የሳበ ሆኖ ተገኝቷል።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካስመረቃቸው ተመራቂዎች መካከል ደግሞ የ70 ዓመቱ ተመራቂ አዛውን የበርካቶችን ቀልብ የሳበ መሆኑም ተነግሯል።
የ70 ዓመቱ አዛውንት አቶ ዓሊ ሳፋ ከቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲው የ9ኛ ዙር ተመራቂዎች ልዩ ተሸላሚ ሆነዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከ35 ዓመት በፊት እንዳገኙ ያስታወሱት አዛውንቱ፣ ለትምህርት ባላቸው ፍቅር የተነሣ የዕድሜያቸው መግፋት ሳይገድባቸው በ70 ዓመታቸው ዛሬ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመቀበል መብቃታቸውን ገልጸዋል።
“የዕድሜዬ መግፋት ከትምህርት ፍላጎቴ አላስቀረኝም” ያሉት አቶ ዓሊ ሳፋ፣ ስምንት ልጆች እና አራት የልጅ ልጆች አያት መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ልጆችን በማሳደግ እና በማስተማር ኃላፊነት የተነሣ ከሚወዱት ትምህርት ለዓመታት ርቀው ቢቆዩም ትምህርት ዕድሜ አይገድበውም እንዲሉ ሁኔታዎች በተመቻቹላቸው ጊዜ ለመማር ሳይሰንፉ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከተቀበሉ ከ35 ዓመታት በኋላ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ በቅተዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በሙያቸው አገራቸውን ያገለገሉት አዛውንቱ አቶ አሊ በጡረታ ላይ ቢሆኑም ትምህርት ቤት ለመሄድ ያገዳቸው ነገር የለም።
በመሆኑም ቡሌሆራ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ዕውቀት ገብይተው በማርኬቲንግ ማኔጅመት በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል።
“ትምህርት ለዚህች ዓለም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዓሊ ሳፋ እውቀት ዕድሜ አይገደበውም” ብለዋል።
በተለይ ልጆች እንዲማሩ ከመገፋፋት ጎን ለጎን ተምሮ አረአያ መሆን ትውልድ ለመቅረጽ ወሳኝ እንደሆነ በመግለጽ ምክራቸውን ለግሰዋል።