ቻይናዊው "ሚሊየነር" እዳቸውን ለመመለስ መንገድ ላይ ምግብ መሸጥ ጀምረዋል
ከአመታት በፊት በርካታ ምግብ ቤቶች የነበራቸው ጎልማሳ ከሚሊየነርነት ወደ 6 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ባለእዳነት ያደረሳቸውን ንግድ አቁመው ወደቀደመ ሙያቸው ተመልሰዋል
የ52 አመቱ ታንግ ጂያን "ህይወት ውጣ ውረድ አያጣትም፤ ቁምነገሩ ከችግር መውጫ መንገድን መዘየዱ ነው" ብለዋል
ከ16 አመታት በፊት በቻይናዋ ዥጂያንግ ግዛት ሃንግዙ ከተማ በርካታ ምግብ ቤቶችን የከፈቱት ታንግ ጂያን በአጭር ጊዜ ሚሊየነር ሆነዋል።
ቢዝነሳቸውን ወደ ግዛቷ የተለያዩ ከተሞች አስፋፍተውም በ36 አመታቸው አንቱታን ያተረፉ ንግድ አዋቂ ተባሉ።
ታንግ ሃብት በሃብት ላይ መደረብ ሲይዙ ግን ሙያቸውን ናቁት።
በፈረንጆቹ 2005 በማያውቁት የንግድ ዘርፍ መሰማራት ሲጀምሩም ዩዋን ፊቷን አዞረችባቸው።
ቢመከሩ ቢገሰፁ አሻፈረኝ ያሉት ታንግ፥ ከምግብ ቤቶቹ ገቢ በእጥፍ ሃብት አካብትበታለው ብለው ያመኑበት የመሬት ማስዋብ ቢዝነስ ለኪሳራ ጣላቸው።
አዲሱ ስራ ለኪሳራ እየዳረጋቸው መሆኑን እየተመለከቱ እንኳን ወጪያቸውን ገፉበት እንጂ ቆም ብለው አላሰቡም፤ የገባቸው ሁሉም ነገር ከጨለመ በኋላ ነበር።
ወደ ቢሊየነርነት ያሸጋግረኛል ያሉት ቢዝነስ ሁሉንም ምግብ ቤቶች፣ መኖሪያ ቤታቸውን እና መኪናቸውን እንዲሸጡ አስገደዳቸው።
በዚህም አላበቃም የ46 ሚሊየን ዩዋን ወይም የ6 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር እዳ አስታቀፋቸው።
ታንግ ግን እጅ አልሰጡም፤ ወደሚያውቁት የምግብ ንግድ ተመልሰዋል።
አዲስ ምግብ ቤት መክፈቻም ሆነ መከራያ ገንዘብ የሌላቸው የቀድሞው ሚሊየነር መንገድ ዳር በፍጥነት የሚደርስ ምግብ መሸጥ ጀምረዋል።
እጅ የሚያስቆረጥም ምግብ እየሰራሁ እዳዬን ለመመለስ ተዘጋጅቻለሁ የሚሉት የ52 አመቱ ታንግ፥ የማውቀው ስራ ተገቢውን ዋጋ ይከፍለኛል፤ እዳዬንም እመልሳለሁ ብለዋል።
"ስንወለድ ምንም አልነበረንም፤ ታዲያ ከዜሮ ለመጀመር ለምን እንፈራለን?" ያሉት ታንግ ፥
ይቺ አለም ውጣ ውረድ አያጣትም ስለዚህ ችግር ሲገጥመን መውጫ መንገዱን ማሰብ፣ ከምንም ነገር ተነስቶ መለወጥ እንደሚቻል ማመን እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለብንም" ሲሉም ተደምጠዋል።
በህይወታችን ለሚገጥመን ፈተና መሸነፍ የለብንም የሚል የህይወት ምክራቸውን የለገሱት ጎልማሳ በቻይናውያን እየተወደሱ ነው።
የፅናት ተምሳሌት ናቸው፤ የዜሮ ሳይሆን ከእዳ መነሳትም ለስኬት እንደሚያደርስ አሳይተውናል የሚሉና ሌሎች አበረታች አስተያየቶች እየደረሷቸው ይገኛሉ።
የቀድሞው ሚሊየነር መንገድ ዳር ስራቸውን ሲከውኑ የሚያሳየውን ተንቀሳቃሽ ምስልም በርካቶች እየተቀባበሉት ነው።