ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ከተነጠለች ጊዜ ጀምሮ ከ12 ሺህ በላይ ሚሊየነሮች ወደ ሌላ ሀገራት ተሰደዋል ተብሏል
በአንድ ዓመት ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ ሚሊየነሮች ከብሪታንያን መሰደዳቸው ተገለጸ።
ብዙ የዓለማችን ሀገራት ባለጸጋዎች ወደ ሀገራቸው መጥተው እንዲኖሩ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉላቸው የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ።
የዓለማችን ባለጸጋ ግለሰቦች እና ተቋማትም የተሻለ ደህንነት እና ምቾት ወደሚሰጧቸው ሀገራት ይኮበልላሉ።
የእንግሊዝ ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ሰሜን አየርላንድ ስብስብ የሆነው ዩኬ ወይም ዩናይትድ ኪንግደም የዓለማችን ባለጸጋዎች ገነት በመባል ትታወቃለች።
ሀገራቱ "የባለጸጋዎች ገነት" የሚለውን ስያሜ ያገኘችው ብዙ የዓለማችን ሚሊየነሮች በዝቅተኛ ወለድ ሀብታቸውን ማስቀመጥ እና ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል ስለተመቻቸላቸው ነበር።
በኢንቨስትመንት ስደት ዙሪያ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው ሄንሌይ ኤንድ ፓርትነርስ የተሰኘው ተቋም ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል።
በዚህ ተቋም ሪፖርት መሰረት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት ከአንድ ሺህ በላይ ሚሊየነሮች ከዩኬ ተሰደዋል።
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት አባልነት መውጣቷ ለሚሊየነሮቹ መሰደድ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም በጥናቱ ላይ ተጠቅሷል።
ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት በህዝበ ውሳኔ ከወጣችበት ከፈረንጆቹ 2016 ጀምሮም 12 ሺህ ሚሊየነሮች ወደ መካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ተሰደዋል ተብሏል።
መቀመጫቸውን ብሪታንያ ያደረጉ ተጨማሪ ሚሊየነሮችን ለመሰደድ እንዳሰቡ ተገልጿል።
የአውሮፓ ጥናት ማዕከል በቅርቡ ባስጠናው ጥናት መሰረትም ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት በመውጣቷ ምክንያት 40 ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን ገልጿል።
የብሪታንያ የበጀት ቢሮ በበኩሉ ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት በመውጣቷ ዓመታዊ እድገቷን በአራት በመቶ እንደቀነሰ ገልጾ እስከ 2031 ድረስ የ100 ቢሊዮን ዩሮ ኪሳራ ያደርሳልም ተብሏል።