ፊሊፒንስ፤ ቻይና አወዛጋቢ በሆነው የውሃ አካል ውስጥ የተገኘን ቁስ ''በኃይል'' ያዘች ስትል ከሰሰች
በቻይና በኃይል ተወሰደ የተባለው ቁስ ከሮኬት ፍርስራሾች ጋር ተመሳሳይነት አለው ተብሏል
ክስተቱ የተከሰተው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ የሦስት ቀን ጉብኝት ከመጀመራቸው ከሰዓታት በፊት መሆኑ ታውቋል
የፊሊፒንስ የባህር ኃይል የቻይና የባህር ጠረፍ ጠባቂ ወታደሮቹ ሁለቱ ሀገራት በሚወዛገቡበት የደቡብ ቻይና ባህር ውሃ ውስጥ ያገኟትን ተንሳፋፊ ቁስ “በኃይል” መያዛቸውን ወቅሷል።
አንድ ከፍተኛ የፊሊፒንስ የባህር ኃይል ባለስልጣን ክሱን ያቀረቡት የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የፊሊፒንስ ደሴት በጎበኙበት ዋዜማ ነው።
የቻይና የባህር ጠረፍ ጠባቂ መርከብ የፊሊፒንስ የጎማ ጀልባ “ማንነቱ ያልታወቀ ተንሳፋፊ ነገር” ሲጎትት “ከለከለ” ተብሏል። የፊሊፒንስ ባህር ኃይል ጀልባዋ ላይ የተጣበቀውን የመጎተቻ መስመር በመቁረጥ ተንሳፋፊውን ቁስ "በኃይል ወሰደ" ብሏል።
በቻይና በኃይል ተወሰደ የተባለው ቁስ በዚህ ወር የቤጂንግ የተካሄደ የሮኬት ትርኢት ከሚመስሉ ተንሳፋፊ ፍርስራሾች ጋር ተመሳሳይ ነው ሲሉ የፊሊፒንስ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ሜጀር ቼሪል ቲንዶግ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ በእሰጣ ገባው የተጎዳ ሰው የለም ማለታቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
በማኒላ የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።
የፊሊፒንስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ጉዳዩን አውቆ ከባህር ውስጥ ህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች ዝርዝር ዘገባዎችን እየጠበቀ ነው” ተብሏል።
ይህ ክስተት የተከሰተው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የሦስት ቀን ጉብኝት ከመጀመራቸው ከሰዓታት በፊት መሆኑ ታውቋል።
ቻይና በየዓመቱ በትሪሊዮን ዶላር የሚገመት የመርከብ መጓጓዣ ንግድ የሚተላለፍበትን መላው የደቡብ ቻይና ባህር ላይ ሉዓላዊነቷን እንዳላት ትናገራለች።