አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያደርጋሉ ተባለ
አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የፊታችን ረቡዕ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተገልጿል
የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ኪን ጋንግ የአፍሪካ ሲዲስን እንደሚመርቁ ተገልጿል።
የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በአዲስ አበባ የተገነባውን የአፍሪካ ሲዲሲ ይመርቃሉ ተባለ።
ባሳለፍነው ሳምንት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው የተሾሙት ኪን ጋንግ የመጀመሪያ የውጭ ሀገራት ጉብኝታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ያደርጋሉ ተብሏል።
በአሜሪካ የቀድሞው የቻይና አምባሳደር የነበሩት ጋንግ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ ወደ አፍሪካ እንደሚጓዙ አስታውቀዋል።
ሚንስትሩ በቀጣዩ ረቡዕ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማሀማት ጋር እንደሚወያዩ ህብረቱ በድረገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋንግ ሙሉ በሙሉ በቤጂንግ ድጋፍ እየተገነባ ያለውን የአፍሪካ በሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል የመጀመርያ ዙር ግንባታን ይመርቃሉም ተብሏል።
እንዲሁም የሁለተኛውን ዙር የማዕከሉን ግንባታ እንደሚያስጀምሩ ሲገለጽ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነሮች እና ሌሎች ሀገራት ተወካዮች ጋርም እንደሚወያዩ ተገልጿል።
አዲሱ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ እና ሌሎች ከፍተኛ መሪዎች ጋር እንደሚወያዩም ይጠበቃል።
የአፍሪካ ሲዲሲ ግንባታ በፈረንጆቹ 2020 ላይ የተጀመረ ሲሆን ግንባታው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት መዘግየቱ ይታወሳል።