ህንድ ከ3 ወር በኋላ በህዝብ ብዛት ቁጥር የአንደኛ ደረጃን ከቻይና ትረከባለች ተባለ
የዓለም የወሊድ ምጣኔ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅናሽ ማሳየቱን ተመድ አስታውቋል
እስያና ምዕራብ አውሮፓ ሀገራት በእድሜ የገፉ ህዝብ ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል
ህንድ ከሶስት ወር በኋላ በህዝብ ብዛት ቁጥር የአንደኛ ደረጃን ከቻይና ትረከባለች ተባለ።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስር ያለው የዓለም ስነ ህዝብ ፖሊሲ ባወጣው መረጃ መሰረት ቻይና አሁን ላይ 1 ነጥብ 412 ቢሊዮን ህዝብ በመያዝ ቀዳሚዋ ሀገር ናት።
ጎረቤቷ ህንድ ደግሞ በ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ህዝብ ሁለተኛዋ የዓለማችን ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገር መሆኗንም ይሄው ተቋም አስታውቋል።
ከሚቀጥለው ሚያዝያ ወር ጀምሮ ደግሞ የሕንድ ህዝብ ቁጥር ቻይናን በመብለጥ ቀዳሚዋ ሀገር ትሆናለች ተብሏል። የህንድ ህዝብ ቁጥር ከዓለም ህዝብ ቁጥር የስምንት በመቶ በላይ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ላለፉት 50 ዓመታት እና ከዛ በላይ ዓለምን በህዝብ ብዛት ስትመራ የቆየችው ቻይና የአንድ ልጅ ፖሊሲን በመተግበሯ ምክንያት የህዝብ ቁጥሯ ሊቀንስ እንደቻለ ሮይተርስ ዘግቧል።
ሕንድ ደረጃዋን እያሻሻለች ያለችው በህዝብ ብዛት ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም ሲሆን በኢኮኖሚ አምስተኛዋ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ የነበረችው ብሪታንያ ደረጃዋን ለሕንድ አስረክባለች።
የሕንድ ኢኮኖሚ በፈረንጆቹ 2029 ላይ ሶስተኛው የዓለማችን ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ እንደምትሆንም ተገምቷል።
ሕንድ እና ቻይና ከፈረንጆቹ 1950 ጀምሮ ለዓለም ህዝብ የ35 በመቶ አበርክቶም ነበራቸው።
ዓለም አሁን ላይ የዓለማችን ህዝብ ብዛት ስምንት ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህ አሀዝ በፈረንጆቹ 2080 ላይ ወደ 10 ነጥብ 4 ቢሊዮን ከፍ እንደሚል ትንበያው ያስረዳል።
በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ውስጥ የዓለም ህዝብ ቁጥርን ግማሹን የሚሸፍኑት ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ግብጽ፣ ኢትዮጵያ ፣ ሕንድ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ እና ታንዛንያ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
የዓለም በህይወት የመኖር እድሜ ጣሪያም ከ50 ዓመት በኋላ ወደ 77 ዓመት ዝቅ እንደሚልም ተመድ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።