የቻይና ፖሊስ 150 ድመቶችን ከመታረድ መታደጉን ገለጸ
በቻይና በየዓመቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ ድመቶች እና ውሾች እየታረዱ ለምግብነት ይውላሉ
የምስራቃዊ ቻይና ፖሊስ ድመቶቹ ታርደው ለምግብነት ሊዉሉ ሲል ደርሼ አድኛለሁ ብሏል
የቻይና ፖሊስ 150 ድመቶችን ከመታረድ መታደጉን ገለጸ፡፡
በምስራቃዊ ቻይና ሻንዶንግ ግዛት ጅናን ከተማ 150 ድመቶች ታርደው ለምግብነት ሊዉሉ ሲሉ ደርሼ ታድጌያለሁ ማለቱን የሀገሪቱ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ፖሊስ ከእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ተቋማት በደረሰው ጥቆማ መሰረት ወደ ጅናን ከተማ በማምራት የአካባቢው ነዋሪዎች ንብረት የሆኑ ድመቶችን በማጥመድ እንዲያዙ ተደርገው ለአንድ ሬስቶራንት ታርደው ለምግብነት እንዲውሉ ታቅደው ነበር፡፡
ፖሊስ በስፍራው ከደረሰ በኋላ የነበረውን ክስተት ሲገልጽ ከየቦታው የተሰባሰቡ ድመቶች በአንድ ስፍራ ተቆልፎባቸው የሚያሰሙት ጩኀት ይረብሻል ብሏል፡፡
እነዚህ ከመታረድ ከዳኑት 150 ድመቶች ውስጥ 31ዱ ድመቶች በቻይና ህግ መሰረት ለአደን የማይውሉ ብርቅዩ እና የጫካ ድመት ዝርያዎች ናቸውም ተብሏል፡፡
በቻይና በየዓመቱ 10 ሚሊዮን ውሾች እና አራት ሚሊዮን ድመቶች ለምግብነት በሚል እንደሚገደሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
የውሻ እና ድመት ስጋ ለቻይናዊያን እንደ ውድ እና ጣፋጭ ምግቦች መታየታቸው እነዚህ እንስሳት ላይ ለምን አደን እንደሚደረግባቸው ዋነኛው ምክንያት ነውም ተብሏል፡፡
በየዓመቱ ሀምሌ ወር ላይ በቻይና አብዛኞቹ ከተሞች በየጎዳናዎቹ ላይ የውሻ እና ድመት ስጋ ፌስቲቫል የሚቀርቡ ሲሆን በህይወት ያሉ ውሾች በሸማቾች ፊት እየታረዱ ለሰው ልጆች በምግብነት ይውላሉ፡፡
የውሻ ስጋ ሽያጭ በቻይና አትራፊ እና ተፈላጊ የስራ ዘርፍ ሲሆን ዓለም አቀፍ የእንስሳት ተቆርቋሪዎች እያደረጉት ባለው ጫና ንግዱ እየቀነሰ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምክንያት በቻይና የእንስሳት ስጋን የመመገብ ፍላጎት እንዲቀንስ በማድረግ ላይ ሲሆን አሁንም እነዚህ እንስሳት ታድነው እየታረዱ ነው ተብሏል፡፡