ህወሓት ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ የቱሪዝም ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን መንግስት አስታወቀ
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ዘርፉን እንዲያግዙም ጥሪ ቀርቧል
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ነዋሪዎች ያገኙት የነበረውን 36 ሚሊዮን ብር ማጣታቸውም ነው የተገለጸው
በሽብርተኝነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን ወርሯቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ ቅርሶች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች እና ጥብቅ የማህበረሰብ ስፍራዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ቡድኑ በተለያዩ የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች ያደረሰውን ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት አስመልከተው መግለጫ የሰጡት ሚኒስትር ዴዔታዋ ሰላማዊት ካሳ ጥልቅ ጥናት ቢያስልገውም ከባድ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል፡፡
በትግራይ እንደተደረገው ሁሉ በአማራ እና በአፋርም ተመሳሳይ አይነት የጣምራ ምርመራና ሪፖርት ይደረግ ይሆን ?
እንደ ሚኒስትር ዴዔታዋ ገለጻ ከሆነ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን በቅርስና የቱሪስት መዳረሻ በሆኑ 6 የሃይማኖት ተቋማት፣ 2 የቱሪዝም ድርጅቶች እና በ22 የቱሪዝም አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት፤ ባለሙያዎች ወደስፍራው አቅንተው ባደረጉት ምልከታ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙም ተረጋግጧል፡፡
በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የነበረው የቱሪስት ፍሰት መቆሙን የተናገሩት ዴዔታዋ ፓርኩ ከጎብኚዎች ያገኝ የነበረውን 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር አጥቷል ብለዋል፡፡
ከፓርኩ የቱሪስት እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ህይወትን የሚመሩ ዜጎች በአጠቃላይ ሊያገኙት ይችሉ የነበረውን 36 ሚሊዮን ብር አካባቢ ማጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡
“ይህ ከባድ ማህበራዊ ቀውስ ነው” ነው ሚኒስትር ዴዔታዋ ያሉት፡፡
በመንዝ ጓሳ ጥብቅ የማህበረሰብ ስፍራ፣ በቦረና ሳይንት፣ በወረሂመኑ፣ በጉና እና በአቡነ ዮሴፍ ፓርኮች ከፍተኛ ጉዳት ደመድረሱንም ገልጸዋል፡፡
በአፋር ክልል በቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጉዳት ከመድረሱም በላይ ከዘርፉ ሊገኝ ይችል የነበረ ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ታጥቷል ያሉት ሰላማዊት ማህበረሰቡ ይህን ከመሳሰለው ቁሳዊ ጉዳትም በላይ ለከፍተኛ ስነ ልቦናዊና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች መዳረጉን ተናግረዋል፡፡
ከ3 ለሚልቁ ወራት በህወሓት ቁጥጥር ስር የነበሩት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ለመምጣት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ተከትሎ መንግስት አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፤ ቱሪዝም ኢትዮጵያኑ ሊደግፉ የሚችሉበት አንዱ የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ በመንግስት መያዙን በመጠቆም፡፡
በ‘ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ’ ወደ ሃገራቸው የሚገቡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ይህን “እንዴት ሊደግፉ እንደሚችሉ ሊያስቡበት ይገባል”ም ብለዋል ሚኒስትር ዴዔታዋ፡፡