
እውነተኛ ሰው መስላ አጭበርብራለች የተባለችው ሴት ቪዲዮ ፣ፎቶዎችን እና ድምጿን ሳይቀር ስትልክለት እንደነበር ተገልጿል
እውነተኛ አፍቃሪ ያገኘ መስሎት 28 ሺህ ዶላር የተጭበረበረው ሰው
ስሙ ያልተጠቀሰው ቻይናዊው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዲና በሆነችው ሻንጋይ ከተማ የሚኖር ሰው ነው፡፡
ይህ ሰው ጂአዎ ከተባለች እና በአሜሪካ ትኖራለች ከተባለች ሴት ጋር ለረጅም ጊዜ በኢንተርኔት አማካኝነት ሲያወሩ መቆየታቸውን ተናግሯል፡፡
ይህች ሴት በሻንጋይ ከሚኖረው አፍቃሪዋ ጋር በቪዲዮ እና በድምጽ በየዕለቱ ሲያወሩ ነበር የተባለ ሲሆን በየዕለቱ እንቅስቃሴዋን በፎቶ እያስደገፈች ስትልክለት እና ሲናፍቃት በስልክ እየደወለች በድምጽ ሳይቀር ሲያወሩ እንደቆዩ ተገልጿል፡፡
የራሷ መታወቂያ እና የሕክምና ምርመራ ውጤት ሳይቀር ለአፍቃሪዋ ስትልክለት ቆይታለች የተባለ ሲሆን ለጀመረችው ንግድ ማስፋፊያ እና ቤተሰቦቿን ለማሳከም በሚል ከቻይናዊው 28 ሺህ ዶላር ተቀብላለች ተብሏል፡፡
ሲጂቲቪ የተሰኘው የቻይና መንግስታዊ ሚዲያ እንደዘገበው ከሆነ ግለሰቡ በመጨረሻም እያወራት የነበረችው ሴት ስትጠፋበት እና ገንዘቡን እንደተበላ ሲያውቅ ጉዳዩን ለፖሊስ እንዳሳወቀ ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ ፖሊስ ባደረገው ክትትልም ግለሰቡን ስታወራው ነበር የተባለችው ሴት እውነተኛ ሳትሆን ሀሰተኛ ምስል በመጠቀም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የተቀነባበረ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡
ቻይናዊው አፍቃሪም 200 ሺህ ዩዋን ወይም 28 ሺህ ዶላር ገንዘቡን ማስመለስ አይቻልም ተብሏል፡፡
ኤአይን ተጠቅመው ማጭበርበር የሚፈጽሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ሜታ ኩባንያ በቅርቡ ለተጠቃሚዎቹ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በርካታ የዓለማችን ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ኤአይን ተጠቅመው ህይወታቸውን እያሻሻሉ ቢሆንም ቴክኖሎጂውን ላልተገባ አገልግሎት የሚጠቀሙ ስላሉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡