ቻይናዊው ቢሊየነር ባኦ ፋን ደብዛው መጥፋቱ ተነግሯል
የታዋቂ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤቱ ፋን ፥ ለቀናት በአካልም ሆነ በስልክ ሊገኝ አለመቻሉን ኩባንያው አስታውቋል
በቻይና የፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤቶች ለወራት ደብዛቸው የመጥፋቱ ጉዳይ እየተደጋገመ ነው
የቻይና ሬኔሰንስ ኢንቨስትመንት ባንክ ባለቤቱ ባኦ ፋን ለቀናት ከእይታ መሰወሩ ተገልጿል።
ቢሊየነሩ ፋን ደብዛው መጥፋቱን ኩባንያው ቻይና ሬኔሰንስ ነው ይፋ ያደረገው።
ቢሊየነሩ ለአይንም ሆነ ለጆሮ ከተሰወረ ስንት ቀናት እንደተቆጠሩ ግን አልተገለጸም።
“ባኦ የት እንደሚገኙ መረጃ የለንም፤ ከእይታ የተሰወሩበት ምክንያትም ከስራ ጋር የተያያዘ ይሁን ሌላ ግልጽ አይደለም” ብሏል ኩባንያው ባወጣው መግለጫ።
ዲዲ እና ማይተን የተሰኙ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ባለቤት የሆነው ባኦ ፋን በቻይና የባንክ ኢንዱስትሪ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ መሆኑን የሬውተርስ ዘገባ ያሳያል።
የባኦ ፋን መጥፋት ከዚህ ቀደም በቤጂንግ ተደጋግሞ የታየውን የቴክኖሎጂ ኩባንያ ባለቤቶች ለወራት ደብዛቸው መጥፋትን የሚያስታውስ ሆኗል።
ባለፉት ጥቂት አመታት ከቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል የተባሉ ከግማሽ ደርዘን በላይ የቻይና ቢሊየነሮች ለቀናት ብሎም ለወራት ደብዛቸው ጠፍቶ እንደነበር ፎርብስ አስታውሷል።
አብዛኞቹም ከታክስ ማጭበርበር እና ሙስና ጋር በተያያዘ ይከሰሱ እንደነበር ያነሳው ዘገባው፥ ዋናው ምክንያት ግን ቤጂንግ በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ የያዘችው ጥብቅ አቋም ነው ይላል።
የቻይናው ዋረን ቡፌት እየተባሉ የሚጠሩት ጉኣ ጉዋንቻንግ በፈረንጆቹ 2015 ለቀናት ደብዛቸው ከጠፉ ሰዎች መካከል ይገኙበታል።
በ2020ም የአሊባባው ባለቤት ጃክ ማ ለሶስት ወራት ከህዝብ እይታ ተሰውሮ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በቻይና የኢንተርኔት ንግድን የሚያቀላጥፉ በርካታ ድረገጾች ባለቤት የሆነው ቢሊየነሩ ባኦ ፋን የተሰወረበት ምክንያት አልታወቀም።
ሰፊ የጸረ ሙስና ትግል ላይ ነኝ የሚለው የፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ አስተዳደርም ምንም አይነት መረጃ አልሰጠም።
ባኦ ፋን ከኢንቨስትመንት ባንኩ ባሻገር የማስታወቂያ፣ የኦንላይን ምግብ ማቅረቢያ እና ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ ድረገጾች ባለቤት ነው።
በቻይና የቴክኖሎጂ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ትልቅ ድርሻ ያለው ባኦ ፋን፥ ፎርብስ በ2021 ባወጣው መረጃ መሰረት ከ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ሃብት አለው። ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት አመታት ያስመዘገበው ሃብት ከቻይና ትልልቅ ባለጸጎች ጎራ ሊያሰልፈው የሚችል ነው ተብሏል።