የጠፉ ሰዎችን መንግስት እንዲያፈላልግላቸው ቤተሰቦቻቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው
በሜክሲኮ ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በለጠ፡፡
በሰሜን አሜሪካዋ ሜክሲኮ በታቀደ እና በተደራጀ መንገድ የሰዎችን ደብዛ ማጥፋት እየጨመረ መምጣቱን የሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት በሜክሲኮ ከፈረንጆቹ 1964 ዓመት ጀምሮ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ ደብዛቸው የጠፋ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቤተሰቦቻው የተሰወሩባቸው ሰዎችም መንግስት የጠፉ ቤተሰቦቻቸውን እንዲፈልግላቸው የጠየቁ ሲሆን በተለይም ባለፉት 20 ዓመታ ውስጥ ደብዛቸው የሚጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡
ከ20 ዓመት በፊት በሜክሲኮ ደብዛቸው ጠፍቷል በሚል የተመዘገቡ ሰዎች ቁጥር 73 ሺህ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ቁጥሩ ከ100 ሺህ አልፏል ተብሏል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ቡድኖች እና ቤተሰቦቻቸው የጠፋባቸው ሜክሲኳዊያን መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡
አራት ዓመት በፊት ልጇ ደብዛው የጠፋባት እንድ ሜክሲኳዊ እናት እንዳለችው ሁኔታው ግራ እንደሚያጋባ ገልጻ የቤተሰባቸው አባል የጠፋባቸውን ሰዎች የሚረዳ በጎ አድራጎት ድርጅት ማቋቋሟን ተናግራለች፡፡
መንግስት የዜጎች ደብዛ መጥፋት ምንም አያሳስበውም የምትለው ይህች እንስት ጉዳዩ የቀድሞው የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት ፊሊፕ ካልዴርሰን አደገኛ እጽ የሚነግዱ ማፊያዎችን ለማደን ጦር ከላኩበት 2007 ጀምሮ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግራለች፡፡