ለፈተና አይበገሬዋ ሚስት ለ10 አመት ኮማ ውስጥ የቆየ ባሏ ሲነቃ ተመልክታለች
በ2014 በገጠመው የልብ ድካም ኮማ ውስጥ የገባውን ባሏን ተስፋ ሳትቆርጥ ስትንከባከብ ቆይታ የድካሟን ፍሬ ለማየት በቅታለች
ቻይናዊቷ ሚስት ለትዳር አጋሯ ያሳየችው ፍቅርና እንክብካቤ በበርካቶች ተወድሷል
በቻይና ለ10 አመታት ኮማ ውስጥ የነበረው ግለሰብ ምስጋና ለተወዳጅ ሚስቱ ይግባና ነቅቷል።
በምስራቃዊ ቻይና አንሁይ በተባለችው ግዛት ነዋሪ የሆነችው ሰን ሆንግሻይ ባሏ በ2014 በገጠመው ድንገተኛ የልብ ድካም ኮማ ውስጥ ይገባል።
በአጭር ጊዜ ከኮማ ይወጣል፤ የቤተሰቡም ስጋት ይወገዳል ተብሎ ቢጠበቅም ምን እየተካሄደ እንደሆነ በውል መረዳትና መግለጽ የማይችለው ባል 10 አመታት ኮማ ውስጥ ይቆያል።
ከሰሞኑ ግን ሰን ለድፍን አስር አመታት በተስፋ የጠበቀችው፤ በብዙ የደከመችለት ጉዳይ ፍሬ አፍርቶ የምትወደውና የሁለት ልጆቿ አባት ነቅቷል።
ያለፉትን አመታት እንዴት እንዳሳለፈች በእምባ ታጅባ ስትነግረው የሚያሳይ ምስልም ተለቋል።
“ምንም እንኳን በጣም ቢደክመኝም ቤተሰባችን ወደቀድሞው ደስታው እንዲመለስ የተከፈለ መስዋዕትነት አድርጌ እወስደዋለሁ” ስትልም ዳዋን ለተሰኘው የቻይና መገናኛ ብዙሃን ተናግራለች።
የሰን ባል ረጅም አመት ኮማ ውስጥ መቆየቱን ተከትሎ የሚስቱ ድጋፍ እጅግ ወሳኝ ነበር።
የሰውነት አካሉን ማዘዝ ስለማይችል አይንቀሳቀስም፤ ይህም ካለሚስቱ ድጋፍ መጸዳዳት እንኳን እንዳይችል አድርጎታል።
አይኑ በሂደት በከፊል መገለጥ መጀመሩ ተስፋየን እያለመለመው ሄደ የምትለው ሰን ከጊዜ ወደ ጊዜ ህመሙ እየበረታ ፈተናዋን ቢያበዛባትም እስከህይወቱ ፍጻሜ አብራው ለመቆየት ቃል ለገባችለት ባሏ ሙሉ ጊዜዋን ሰጥታ ያለመሰልቸት ተንከባክባዋለች።
የ84 አመቱ የታማሚው አባትም የዚህ ምስክር ናቸው።
“ሰን የልጄ ሚስት ብትሆንም ከሴት ልጄ የተሻለች ልዩ ሰው ናት፤ ከእርሷ ጋር ማንም አይወዳደርም” ሲሉ ለልጃቸው ያሳየችውን ወደር የለሽ ፍቅር እና እንክብካቤ አድንቀዋል ብሏል ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት በዘገባው።
ለ10 አመት የባሏን ህመም የተጋራችውና ፍቅሯን በተግባር ያሳየችው ቻይናዊት ሚስት ለልጆቿ አርአያ ሆናለች።
ከኮማ ከወጣ ባሏ ጋር የተነሳችው ምስልም በቻይና ማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እየተዘዋወረ ነው።
በርካቶች “እውነተኛ ፍቅር ማለት ይህ ነው” እያሉ አድናቆታቸውን እየገለጹላት ይገኛሉ።