ግዙፍ “የሚስት አፋልጉኝ ማስታወቂያ” የለጠፉት አሜሪካዊ ውሃ አጣጬ ከወዴት አለሽ እያሉ ነው
የ70 አመቱ አዛውንት ማስታወቂያውን የተመለከቱ ከ400 በላይ ሰዎች ቢደውሉልኝም እስካሁን መስፈርቴን የምታሟላውን አላገኘሁም ብለዋል
ፍቅር የተራቡት አሜሪካዊ አደባባይ ላይ ላሰቀሉት ማስታወቂያ በሳምንት 320 ፓውንድ ይከፍላሉ
ብቸኝነት ያሰለቻቸው የ70 አመት አዛውንት የትዳር አጋር ፍለጋ ላይ ናቸው።
ምኞታቸውን እውን ለማድረግ በሳምንት 320 ፓውንድ የሚከፈልበት ግዙፍ ቢልቦርድ ላይ ምስላቸውን፣ ስልካቸውን እንዲሁም የኢሜል አድራሻቸውን ያሰፈሩበትን ማስታወቂያ እንዲለጠፍ አድርገዋል።
“ብቸኛ ነኝ፤ የትዳር አጋር እፈልጋለሁ፤ የምፈልጋትን አይነት ሴት ካገኘሁ የመኖሪያ አድራሻዬን ለመቀየር ዝግጁ ነኝ” ይላል ማስታወቂያው።
በቴክሳስ ነዋሪ የሆኑት ኤአይ ጊልበርቲ ማስታወቂያው ከተለጠፈ በኋላ በሁለት ሳምንት ብቻ ከ400 በላይ የስልክ ጥሪዎች እንዲሁም ከ50 በላይ የኢሜል መልዕክቶች እንደደረሳቸው ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ አንዳቸውም መስፈርታቸውን የሚያሟሉ ሆነው እንዳላገኟቸው ነው የገለጹት።
ታማኝነት፣ ሃቀኝነት እና ትህትና የማልደራደርባቸው ቀይ መስመሮች ናቸው የሚሉት ጊልበርቲ፥ ኣአብዛኞቹ የስልክ ጥሪዎች ያላቸውን ሃብት ታሳቢ ያደረጉና ወጪዎችን ሸፍኑልኝ የሚሉ መሆናቸውን መናገራቸውን ሚረር አስነብቧል።
ከቀድሞ የትዳር አጋራቸው አንድ ልጅ ያገኙት አዛውንት፥ “ትክክለኛዋን ሴት ካገኘኋ አይን አይኗን እያየው ምላሿን ማየት እፈልጋለሁ፤ የልቤን መሻት የምታሟላውን ካገኘሁ ወደ አውሮፓ ጠቅልዬ ለመጓዝም ዝግኙ ነኝ” ብለዋል።
ጥሩ አድማጭና ለንግግር ክፍት መሆናቸውን የሚያነሱት ጊልበርቲ፥ ከ2015 ወዲህ በብቸኝነት ኑሮን እየገፉ መሆኑ እንደከበዳቸው ያነሳሉ።
እንደ እድሜያቸው ሳይሆን በጥሩ አቋም ላይ መገኘታቸውንና ጥሩ የጡረታ ገቢያቸውንም እንደ ማጫ አቅርበውታል።
የቀድሞ የትዳር አጋራቸውን በ26 አመት እንደሚበልጧቸው በማውሳትም ለእድሜ ልዩነት ቦታ እንደማይሰጡ ይገልጻሉ።
በግዙፍ ማስታወቂያ የትዳር አጋር ፍለጋቸው ዝነኛ እንዲያደርጋቸው መሻታቸውን ሳይሸሽጉም አንድ ቀን የፈለጓትን አይነት ሚስት እንደሚያገኙ ተስፋ አድርገዋል።
በአሜሪካ የትኛውም ግዛት በአካል በመጓዝ፤ በአውሮፓ የሚገኙትን ደግሞ በዙም (በበይነ መረብ) በማግኘት ውሃ አጣጫቸውን እንደሚፈልጉም ነው የተናገሩት።