ቮስቶክ 2022 ልምምድ ላይ 50 ሺህ ወታደሮች እና የተለያዩ ጦር መሳሪያዎች ይሳተፋሉ
የቻይና ጦር በሩሲያ ግዛት ውስጥ በሚካሄደው ወታደራዊ ልምምድ ላይ ለመሳተፍ በትናትናው እለት ሞስኮ መድረሱ ተነግሯል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ትናንት በለቀቀው የቪዲዮ ምስል ላይ የቻይና ጦር ለግዙፉ ወታደራዊ ልምምድ ዝግጅት ሩሲያ መድረሱን ያሳያል።
ቮስቶክ 2022 የሚል መጠሪያ የተሰጠው ወታደራዊ ልምምድ ከነገ ጀምሮ ለ7 ቀናት በሩቅ ምስራቅ ሩሲያ እና በጃፓን ባህር ላይ የሚካሄድ መሆኑ ተነግሯል።
በዚህ ወታደራዊ ልምምድ ላይ አዘጋጇ ሩሲያን ጨምሮ ቻይና፣ ቤላሩስ፣ ታጃኪስታን፣ ህንድ፣ ሞንጎሊያ እና ሌሎችን ሀገራት ይሳተፋሉ ተብሏል።
ከሀገራቱ የተውጣጡ 50 ሺህ ወታደሮች በልምምዱ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን፤ ከ5000 በላይ የተለያዩ አይነት የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሏል።
ከጦር መሳሪያዎቹ መካከልም 140 የጦር አውሮፕላኖች እና 60 የጦር መርከቦች እንደሚገኙበትም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።
በልምምዱ ላይም የሩሲያ አየር ወለድ ወታደሮች፤ የረጅም ርቀት ቦምብ ጣይ ጄቶ እንዲሁም የጦር ካርጎ አውሮፕላኖች ከሌሎች ሀገራት የጦር መሳሪያዎች ጋር በመሆን እንደሚሳተፍም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
በዚህ የጦር ልምምድ ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ቻይና የአሁኑ የጦር ልምምድ ከወቅቱ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ጋር እንደማይገናኝ መግለጿ ይታወሳል።
ይህ የጋራ የጦርነት ልምምድ በሩሲያ እና ቻይና ድንበር አቅራቢያ ካቦራቭስክ በሚባል ስፍራ እንደሚካሄድ የሩሲያ መከላከያ መረጃ ያወጣው መረጃ ያስረዳል።