አሜሪካ ከ1984 ጀምሮ 100 ሚሊየን ዶላር ተፈላጊዎችን ለጠቆሙ ግለሰቦች ከፍላለች
አሜሪካ አቡ አይመን አልማስሪን ለጠቆመ አምስት ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች።
አሜሪካ የመን በሚገኘው ኢምባሲዋ በኩል ባወጣችው መግለጫ ኢብራሂም አል ባና በሚባል መደበኛ ስሙ የሚጠራውን ግለሰብ ለጠቆመኝ 5 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ብላለች።
አልቃይዳ በተሰኘው የሽብር ቡድን ውስጥ የአረብ ባህረ ሰላጤ ክንፍ መሪ የሆነው አልባና አቡ አይማን አልማስሪ በሚልም ይጠራል ተብሏል።
አልባና ወይም አልማስሪ ከአልቃይዳ መሪዎች መካከል አንዱ ሲሆን በተለይም በየመን እና አካባቢው የሚደርሱ የአልቃይዳ ጥቃቶችን በመምራት ይታወቃል ተብሏል።
ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ በአሜሪካ የሚፈለገው አልማስሪ አልቃይዳን ከመሰረቱ ግለሰቦች መካከል በህይወት ያለ ብቸኛው የድርጅቱ መሪ እንደሆነ ተገልጿል።
አልማስሪ በዜግነቱ ግብጻዊ እንደሆነ የሚገለጽ ሲሆን አልቃይዳን ከመቀላቀሉ በፊት በየመን የግብጽ እስልማቂ ጅሀድ ድርጅት መሪ ነበርም ተብሏል።
አልቃይዳ የሽብር ቡድን በአሜሪካ መንግሥት በውጭ ሀገራት አሸባሪነት የተፈረጀ ሲሆን መሪዎቹም ታድነው ይያዛሉ አልያም በአሜሪካ እና አጋሮቿ ጦር ይገደላሉ።
በዚህም መሰረት አሜሪካ ከፈረንጆቹ 1984 ጀምሮ በአሸባሪነት በተፈረጁ የሽብር ቡድን መሪዎችን ለመያዝ ሲባል ያሉበትን ለጠቆሙ ሰዎች 100 ሚሊዮን ዶላር መክፈሏም ተገልጿል።
በአጠቃላይ ባለፉት 39 ዓመታት ውስጥ 100 ሚሊዮን ዶላር ለጠቋሚዎች የከፈለችው አሜሪካ 70 የተለያዩ የሽብር ቡድን አመራሮችን ገድላለች።